የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የደጃዝማች ኩምሳ ሞረዳ ቤተመንግስት የጥገናና የመልሶ ማልማት ስራ ለማከናወን ከቢዋይ ኤም ቲ ኮንትራክተር ጋር የውል ስምምነት ተፈራረመ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በውል ስምምነቱ ላይ እንደገለፁት ቤተ መንግሥቱ ጥንታዊና ታሪካዊ መሆኑን ጠቅሰው ለረዥም ዓመታት እድሳት ሳይደረግለት ፣ በቱሪዝሙ ዘርፍ አገልግሎት ሳይሰጥ መቆየቱ አብራርተዋል።
ቅርሱ ከጥንት የኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የተያያዙ ስፍራዎችን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ከተመረጡ ስፍራዎች አንዱ መሆኑን ፣ጥገናው ቅርሱ የነበረውን አሻራና ይዘት በጠበቀ መልኩ የቅርስ ጥገና መርሆዎችን በተከተለ መንገድ በጥንቃቄ መከናወን እንዳለበት የጥገና ስራው በተያዘለት የሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ጥራቱን ጠብቆ መጠገንና ለሃገር ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መሆን እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ደጃዝማች ኩምሳ ሞረዳ በከሬ ከ1881ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1916 ዓ.ም. ድረስ የቀድሞ ወለጋ ጠቅላይ ግዛትን ያስተዳድሩ ነበር ፡፡ ንጉሡ ቤተመንግስታቸውን የመሠረቱት 1830 ዓ.ም. ሲሆን ይህ አስደናቂ ቤተመንግስት ያረፈበት ቦታ ስፋቱ 2.5 ሄክታር የሚያካልል ነው፡፡ በቅጥር ግቢው ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ተደርገው የተገነቡ የተለያዩ ቤቶች ሲኖሩ በአጠቃላይ ቅጥር ግቢው አምስት በሮች አሉት፡፡
ይህ ቤተ መንግስት ከአዲስ አበባ በስተ-ምዕራብ በኩል 319 ኪሎ ሜትር ርቀት ነቀምቴ ከተማ ነው የሚገኘው፡፡ ይህም ከከተማዋ መሃል መነሻ ሆኖ በስተ-ምዕራብ በኩል 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከፍ ባለ ውብና ማራኪ ሥፍራ ተንጣሎ እንደሚታይ ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡