የዲጂታል ፋይናንሱን ለማሳደግ ያግዛል የተባለ የ15 ቢሊዮን ብር በጀት ይፋ ተደርጓል፡፡
ሲንቄ ባንክ እና ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል አማራጮችን በማስፋት ማህበረሰቡ የዲጂታል ብድርን በቀላሉ ማግኘት እንዲችል ያደርጋል የተባለ ‘Wabii Digital Finance’ የተሰኘ የዲጂታል ፋይንሲንግ አገልግሎት በይፋ አስጀምረዋል።
ሲንቄ ባንክ፣ ሁለቱ ተቋማት ለፈጠሩት ትስስር ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡ የተነገረ ሲሆን፣ በማስያዣ እና ያለማስያዣ የብድር አቅርቦትን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ተብሏል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ፣ የዲጂታል አካታችነትን ለማረጋገጥ መሰል ትብብሮች አስፈላጊ መሆናቸውን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገልጸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌብር በኩል ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እና ግለሰቦች ለሚያቀርበው ብድር፣ ሲንቄ ባንክ ዋስትና እንደሚሰጥ ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የዲጂታል ፋይናንስን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ የቴክኖሎጂ ቁሶችን የማቅረቡን ስራ ኢትዮ ቴሌኮም ይሰራል ተብሏል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የገጠር ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ እና በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የከተማ ልማት አስተባባሪ አቶ መስፍን መላኩን ጨምሮ ሌሎችም የተቋማት ከፍተኛ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በበላይነህ ፍስሃ