ባለፉት አመታት አደጋ ተጋርጦበት የነበረው የጀጎል ግንብ በተከናወነለት መልሶ የማልማት ስራ ቅርሱን ዳግም የቱሪዝም ማዕከል ማድረግ መቻሉን የሀረሪ ክልል ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የሀረሪ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ቅርሱ ከዚህ ቀደም ለነዋሪዎች ምቹ እንዳልነበር ጠቁመው በተጨማሪም አደጋ ተጋርጦበት እንደነበር አስታውሰዋል።
ሆኖም ተጋርጦበት የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ቅርሱ የቱሪዝም ማዕከል እየሆነ መምጣቱን አክለዋል።
ይህ ይሆን ዘንድ በተለይም በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ስራዎች ቅርሱን እንደታደጉት ገልጸዋል።
ንፁህ ያልነበሩ ስፍራዎች እንዲለሙ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን 7.1 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እንዲለሙ መደረጉ ተመላክቷል።
ልማቱ የአካባቢውን ጸጋዎች በመጠቀም አካባቢውን እንዲገልጽ ተደርጎ የተከናወነ መሆኑም ተገልጿል።
በተጨማሪም በሶስተኛው ምዕራፍ 5.1 ኪሎሜትር መንገድ እየተሰራ ይገኛልም ተብሏል።
በልማት ስራው ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል እየተሳተፉበት መሆኑም ተመላክቷል።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ታሪካዊ መዳረሻዎችን ከዘመኑ ጋር እንዲጣጣሙ በማድረግ እየለሙ መሆኑን ገልጸዋል።
ታሪካዊዉን የጀጎል ግንብ የጎበኙት ሚኒስትር ድኤታው የቱሪዝም ዘርፍ ባለፉት አመታት በልዩነት ትኩረት ተሰጧቸው አየተሰራባቸው ከሚገኙ ዘርፎች መካከል መሆኑን ተናግረዋል።
ነባር ታሪካዊ መዳረሻዎችን አሻራቸውን ጠብቆ ማደስ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መገንባት በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በሃብታሙ ሙለታ