
AMN – ታኅሣሥ -3/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው በኢትዮዽያ የቻይና አምባሳደር ከሆኑት ቼይ ሃይ እና ከሲጂሲኦሲ ግሩፕ (CGCOC group) በተገኙበት የገርቢ የመጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታን በፍጥነት ማስጀመር በሚቻልበት መንገድ ዙሪያ ጋር ተወያይተናል ብለዋል::
የገርቢ የመጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክት በ2008 ዓ.ም ከኤግዚም ባንክ በተገኘ ድጋፍ ይገነባል ተብሎ የታቀደ ቢሆንም ብድሩ እስከ ዛሬ ባለመለቀቁ ምክንያት ሳይጀመር በመዘግየቱ ከተማው አስተዳደር በራሱ በጀት ለመገንባት ወስኗል ብለዋል ።
በከተማዋ ያለውን የውሃ ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም የከተማ አስተዳደሩ በራሱ በጀት ለመገንባት ዛሬ ከቻይና ኤምባሲ እና ከኮንትራክተሩ ሲጂሲኦሲ ግሩፕ ጋር መግባባት ላይ ደርሰናልም ብለዋል::
የከተማችንን የውሃ አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ ከፍተኛ በጀት መድበን በመስራት ላይ የምንገኝ ሲሆን የገርቢ መጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታም ሲጠናቀቅ ይህንን ጥረታችንን ይበልጥ ውጤታማ እንደ ሚያደርግ እና ያለብንን የውሃ ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ይበልጥ እንደሚፈታ እናምናለንም ብለዋል ከንቲባዋ በመልእክታቸው::