AMN – ጥር 23/2017 ዓ.ም
የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ሃሳብ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ እህት ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተካሄዷል፡፡
በጉባኤው ላይ የተገኙ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ እህት ፓርቲዎች አመራሮች፣ በጉባኤው በመታደማቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
በተለይም ጉባዔው በታሪካዊው እና የአፍሪካዊያን ድል ምልክት በሆነው ዓድዋ ድል መታሰቢያ በመካሄዱም ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡
የፓርቲ አመራሮቹ በኢትዮጵያ ብሎም በመዲናዋ አዲስ አበባ ትልቅ ለውጥ መመልከታቸውን የተናገሩ ሲሆን በተለይም በአዲስ አበባ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ከተማዋን ያዘመኑ መሆናቸውን አውስተዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ከመቻል አልፋ ለሌሎች መትረፏ የሚደነቅ እና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ብልጽግና ፓርቲ ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ትልቅ ለውጥ መታየቱን እና ሌሎች ፓርቲዎችም ቃል ገብቶ የመፈጸም ልምዱን የሚማሩበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም ልማትና አካታች አንድነትን ከኢትዮጵያ መማር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ራዕይን ማሳካት አስቸጋሪ መሆኑን በመግለጽ ብልጽግና ፓርቲ ይህንን በመደመር እሳቤ በማሳካቱ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
በኢኮኖሚው ዘርፍም ኢትዮጵያ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት ግንባር ቀደም መሆኗን በመጥቀስ ይህም ራዕይን በተግባር የሚለውጥ አመራር በመኖሩ የመጣ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል መንግስት በትግራይ ክልል ተፈጥሮ ነበረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሄደበትን ርቀትም አድንቀዋል፡፡ ይህም ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋገጠበት ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለቀጣናው ምሰሶ መሆኗን የገለጹት የፓርቲ አመራሮቹ በአህጉር እና በቀጣናው ለሰላምና በኢኮኖሚው ዘርፍ የምታደርገው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰላም ለአፍሪካ አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ ሀገራቱ የብልጽግና ፓርቲን ራዕይና አመራር እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል፡፡
በሰፊና ሁሴን