AMN – ታኅሣሥ 27/2017 ዓ.ም
የገና በዓል ባዛር ላይ እየቀረቡ ያሉ ምርቶች ከሌላው ጊዜ የገበያ ዋጋ አንፃር ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ እንዳላቸው ሸማቾችና ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡
በሌላ በኩል የቁም እንስሳት አቅርቦቱ ከሌላው ጊዜ የተሻለ ቢሆንም መጠነኛ ጭማሪ ማሳየቱን ሸማቾች ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች በተዘጋጁ የገና በዓል ባዛሮች እና በየካ ክፍለ ከተማ ካራሎ አካባቢ በተዘጋጀ የቁም እንስሳት ግብይትና አቅርቦት ምን እንደሚመስል ኤ ኤም ኤን ቅኝት አድርጓል፡፡
የግብርና የኢንዱስትሪ ምርቶችና የቁም እንስሳት በስፋትና በጥራት መቅረባቸውን ነጋዴዎችና ሸማቾች ተናግረዋል፡፡

የበዓል ግብይቱ በተሟሟቀ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን የተናገሩት ሸማቾችና ነጋዴዎች በዋጋ ደረጃም ከሌላው ጊዜ ግብይት ቅናሽ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የቁም እንስሳት አቅርቦቱ በበቂ ሁኔታ መኖሩን የገለጹት ገዥዎችና ነጋዴዎቹ ካለፉት በዓላት አንጻር መጠነኛ የዋጋ ጭማሬ ማሳየቱንም ተናግረዋል፡፡
ኤ ኤም ኤን ቅኝት ባደረገባቸው ቦታዎች ክትትልና ቁጥጥር ሲያደርጉ ያገኛቸው የክፍለ ከተሞች የስራ ኃላፊዎች ምርቶች በበቂ ሁኔታ እንዲቀርቡና ያልተገባ የዋጋ ጭማሬ እንዳያደርጉ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አነስተዋል፡፡
ከባዛር የበዓል ግብይት አቅርቦት በተጨማሪ በየሳምንቱ በሚዘጋጁት የቅዳሜና እሁድ የመገበያያ ስፍራዎችም የመሰረታዊ ሸቀጦች፤ የግብርናና የፋብሪካ ውጤቶች በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት እየቀረቡ ነው፡፡

በሄለን ጀንበሬ