የጋራ ህልም ያስተሳሰረው ትብብር

You are currently viewing የጋራ ህልም ያስተሳሰረው ትብብር

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ሁለቱ ሀገራት አብሮ ለመስራትና ለማደግ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል

                             የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር አቶ በፈቃዱ ዳባ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በሶማሊያ ያደረጉት ጉብኝት ኢትዮጵያና ሶማሊያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በማጠናከር አብሮ ለመስራትና ለማደግ ያላቸውን ፍላጎትና ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር አቶ በፈቃዱ ዳባ ተናግረዋል፡፡

ከትናንት በስቲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞቃዲሾ ሲደርሱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ፣ “ውይይታችን እንደ ሰላም እና ፀጥታ፣ ኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲ እና በጋራ ልንገነባቸው ስለምንችላቸው የመሠረተ ልማት ሥራዎች ያሉ ቁልፍ ጉዳዮችን የተመለከተ ነበር። የአፍሪካ ቀንድ በሀብት የበለፀገ ነው። ለም ምድር፣ የተፈጥሮ ውሃ እና የሰው ኃይል ሀብቶች አሉት። ይሁንና ራሳችንን ለመመገብ ስንቸገር ይስተዋላል። ቀጣናዊ ትስስር የጋራ ህልማችንን እውን ለማድረግ እጅግ ጠቃሚ ነው። ለጋራ እድገታችን ልንጠቀምበት የምንችለው ትልቅ አቅም አለን። በተናጠል ማደግ አንችልም። በጋራ ስንቆም ጠንካራ ነገ እና ብሩህ ተስፋ ይኖረናል። ይኸን እውን ለማድረግ ከሶማሊያ ጋር ለመስራት ዝግጁ ነን” ሲሉ አስፍረዋል፡፡

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በሶማሊያ ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ደግሞ፣ ጉብኝቱ የሁለቱን ጎረቤት ሀገራት ትብብርና ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ በማድረግ ረገድ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው፡፡ ሀገራቱ ወደ አዲስ የትብብር እና የወዳጅነት ምዕራፍ መግባታቸውን ያመላክታል ብለዋል፡፡

ቀደም ብሎ በተለያዩ ሀላፊዎች ደረጃ ሲደረጉ የነበሩ ውይይቶች እና ጉብኝቶች የሀገራቱን ትብብር ይበልጥ መጠናከሩን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በተለይም በፀጥታው ዘርፍ እና በሰላም ማስከበር ኢትዮጵያ ያላትን ተሳትፎ እና የሀገራቱን ትብብር መልክ ያስያዙ ናቸው ብለዋል። ጉብኝቱ ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚና በሌሎች መስኮች ያላቸው ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩንም ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጉብኝትን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት በሰጡት የጋራ አቋም መግለጫ፣ ለጋራ ጥቅም በመካከላቸው ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች ያለውን ትብብር እንዲሁም በመካከላቸው ያለውን መተማመንን ለማሳደግ እንደሚሹ ጠቁመዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች በአንካራው ስምምነት መሰረት የተጀመረውን የቴክኒክ ውይይት እንደሚቀበሉና ገንቢ ውይይትና ትብብር ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሆኑም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

የአንካራው ስምምነት ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ ኢትዮጵያ ወደብ አግኝታ፤ ሁለቱ ሀገሮች በመተባበር አብረው የሚያድጉበትን አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ እና በኒው ጀነሬሽን ዩኒቨርሲቲ ዲፕሎማሲ ያስተማሩት እና በሶማሊላንድ  ሃርጌሳ ዩኒቨርሲቲ ለበርካታ ዓመታት ሰላምና ደህንነት ጉዳዮች እያስተማሩ የሚገኙት አቶ በፈቃዱ ዳባ ለአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ እንደሚሉት፣ ጉብኝቱ በአንካራ የተደረሰውን ስምምነት ወደ ተግባር ለመቀየር ሁለቱ ሀገራት ከመጠራጠርና ፍራቻ ይልቅ አብሮ የማደግና የመስራት ፍላጎታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የመተማመን መንፈስን ለማሳደግ የተደረገ ጥረት በመሆኑ እንደ ትልቅ ጅምር የሚታይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሀዝብ ያላት ሀገር ሆና ወደብ አልባ ናት፡፡ ይህን ያህል ህዝብ ያለው ሀገር የሚያስወጣውና የሚያስገባው የገቢና ወጪ ዕቃ ከፍተኛ ነው፡፡ ሶማሊያ ደግሞ ሰፊ የባህር ጠረፍ መሬት ያላት እንደመሆኑ ኢትዮጵያ ሸቀጦችን በሶማሊያ በኩል ማስገባትና ማስወጣት የምትችልበት የባህር በር ብታገኝ ለሀገሪቱ እድገት ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

በከሰሞኑ መግለጫ፤ በሶማሊያ ብሔራዊ ሰራዊት እና የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት መሪዎች መካከል የተደረሰውን መግባባት ሁለቱ መሪዎችም እንደሚቀበሉና በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ወሳኝ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

የሀገር መሪዎች የሚሰጡት ውሳኔ የመጨረሻ፣ አስተማማኝ፣ በዓለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት እና ተጠያቂነትንም የሚያመጣ ነው የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ በፍቃዱ፣ ከሳምንት በፊት የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሶማሊያ አቻቸው ጋር ያደረጉትን ምክክር ተግባራዊ ለማድረግ፣ እንደ አልሻባብ ያሉ ለቀጣናው ብሎም ለዓለም ሰላም ስጋት የሆኑ አሸባሪዎችን በመዋጋት ሰላም ለማምጣት ያስችላል፡፡ የሁለቱ መሪዎች ውይይት በወንድማማችና እህትማማች ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ሙሉ ፍላጎት እንዳለ ያሳያል፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ በፈቃዱ እንደሚናገሩት፣ ኢትዮጵያና ሶማሊያ በጋራ አብረው ማደግና መበልፀግ የሚችሉባቸው ብዙ እድሎች አላቸው፡፡ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በደም፣ በታሪክና በተፈጥሮ ሀብት የተሳሰሩ ናቸው። ኢትዮጵያ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር፣ ሰፊ የእርሻ መሬትና የተለያዩ የግብርና ምርቶችን የማምረት አቅም ያላት ሀገር ናት፡፡ ወደ ሶማሊያ የሚፈስሱ እንደ ዋቢ ሸበሌ፣ ገናሌ፣ ዳዋ ያሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ደግሞ ከኢትዮጵያ የሚመነጩ ናቸው። በተለይ በደቡብ ሶማሊያ በኩል አድርጎ ወደ ህንድ ውቅያኖስ የሚገባው ውሃ ከኢትዮጵያ የሚመነጭ ነው፡፡ ሶማሊያ አብዛኛው መሬቷ በረሃማ በመሆኑ በሰጥቶ መቀበል መርህ በጋራ ተጠቃሚ የሚሆኑባቸው ብዙ አማራጮች ይኖራቸዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት ድንበር የሚኖሩ ህዝቦች ከግጭት ይልቅ ሰላምና ልማትን ይፈልጋሉ፡፡ በምጣኔ ሀብት መተሳሰራቸው በሀገራቱ ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ ያስችላል፡፡ በመንግስታት ደረጃ ከስምምነት መደረሱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትንም ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ያለንበት ዘመን የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ በቀጣይም ማህበራዊ ሚዲያና የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሞ በጎ ተፅዕኖ በመፍጠር ህዝቦች ተቀራርበው በጋራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባም አቶ በፈቃዱ ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው በትናንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጉብኝት በሁለቱ አጎራባች ሀገራት መካከል ለአንድ ዓመት ያክል የቆየውን የውጥረት ጊዜ ለዝቦ ወደ መደበኛ ግንኙነት መግባቱን ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያና ሶማሊያ በኩል ያለው አሁናዊ ግንኙነት የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ እንዲሁም ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚያስችል የጋራ ስምምነት የተደረሰበት ነው፡፡ ሁለቱ ሀገራት ብሄራዊ ጥቅም ማረጋገጥ የሚያስችሉ የጋራ ስትራቴጂክ ፕሮጀክቶችንም ጭምር ለመጀመር ስምምነት ላይ ደርሰዋል ብለዋል፤ አምባሳደር ነቢያት።

የሶማሊያን ሰላም በዘላቂነት ለማፅናት እየተደረገ ያለው ጥረት፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ጥላ ስር የሚኖራት ሚናም እንደሚቀጥል ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቋል፡፡ ሀገራቱ ከአንካራው ስምምነት ወዲህ በመሪዎች ደረጃ ያደረጓቸው ውይይቶችና ስምምነቶች ለኢኮኖሚያዊ ትብብርና ለቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ ርምጃዎች ናቸው፡፡ ኢጋድ ሰላማዊ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ እና ለቀጣናው ዘላቂ ልማት የሚደረጉ ጥረቶችን ይደግፋልም ብሏል፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ በፈቃዱ ዳባ እንደሚናገሩት፣ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር አብሮ መኖርንና በጋራ መጠቀምን ያስቀደመ ነው፡፡ ከወራት በፊትም በተርኪዬ አደራዳሪነት በአንካራ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በመተው ለጋራ እድገትና ብልፅግና በትብብር ለመስራት፣ ኢትዮጵያ በሶማሊያ የባህር ዳርቻ አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ዘላቂ የባህር መተላለፊያ በምታገኝበት ሁኔታ ላይ የቴክኒክ ውይይቶችን ለመጀመር ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review