የጋራ ትብብር የሚሻው የወል ትልም

You are currently viewing የጋራ ትብብር የሚሻው የወል ትልም

ባሕር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት እሙን ነው፡፡ ከመጓጓዣነት ባሻገር ሰፊ የብዝሃ ህይወት መኖሪያ እና ግዙፍ የምጣኔያዊ ሀብት ዕድገት ምንጭም ነው፡፡ ባሕር በሀገራት መካከል እንደ ድልድይ በማገልገል ልዩ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ያስገኛል፡፡ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተጽዕኖ ከማሳደር አንፃርም ልዩ ዕድል ይሰጣል፡፡ በጥቅሉ የባሕር በር ያላቸው ሀገራት ከሌላቸው ሀገራት ጋር ሲነፃፀሩ በጣም ከፍ ያለ ተጠቃሚነት እንዳላቸውም ይነገራል፡፡

ከ55ቱ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ 16ቱ የባሕር በር የሌላቸው እንደሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ፤ እነዚህም ቦትስዋና፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ቡሩንዲ፣

መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ቻድ፣ ኢትዮጵያ፣ ሌሶቶ፣ ማላዊ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ስዋዚላንድ፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ መሆናቸውን በአፍሪካ ኢኮኖሚና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ስራዎችን በማህበራዊ ሚዲያ በማሰራጨት የሚታወቀው ጂኦ ኤክስፕሮ (GEO EXPRO) የተሰኘ ተቋም ይፋ ያደረገው መረጃ ያመላክታል፡፡

የባሕር በር አልባነት ከዓለም ገበያዎች መገለልና ከፍተኛ የመጓጓዣ ወጪዎችን ያስከትላል፡፡ ወደብ በሌለባቸው በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት አጠቃላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ስለመሆኑ የዓለም ባንክ መረጃም ያመለክታል፡፡

ከዚህ ቀደም ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር  አ?? ???? ????? ???? ?? ?????? ??? ???????ደም ካሚል፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት በሳል ዲፕሎማሲያዊ አካሄዶችን መከተል እና ያሉትን ሰላማዊ አማራጮች ሁሉ አሟጥጦ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የባሕር በር ለኢትዮጵያ ከንግድ ባለፈ የደህንነት እና የልማት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደገለፁት፣ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር የማግኘት ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሕጋዊና ሞራላዊ መብት እንዳላትና የትውልድ ግዴታም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያትም የኢፌዴሪ መንግስት የተለያዩ ሀገራት ከርቀት በመምጣት በቀይ ባሕር የጦር ሰፈር ማቋቋም ደረጃ እየደረሱ ባሉበት ሁኔታ ኢትዮጵያ እጇን አጣጥፋ እንደማትቀመጥና በባሕር በር ዙሪያ አማራጭ መንገዶችን እየፈለገች ስለመሆኑ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ይህንንም ተከትሎ  ጠቅለይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳሉት አሁን ላይ የባሕር በር ጥያቄን ማንሳት ነውርነቱ ቀርቶ በፖለቲከ ምህዳር ውስጥ ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ሊነሳ የሚገባው ወሳኙ ጥያቄ የባሕር በር ጉዳይ የአዲሱ ትውልድ የበኩር ጥያቄው ሆኖ እንዲቀጥል ትውልዱ በተለይም የምሁራን ሚና ምን ሊሆን ይገባል? የሚለው ነው፡፡

የዓለም አቀፍ እና ፖለቲካል ሳይንስ ምሁር የሆኑት አቶ መሐመድ በሽር እንደሚሉት ምሁራን የሀገሪቱን የዕድገት ጉዞ ለማፋጠን እና የዜጎችን ዘርፈ-ብዙ ተጠቃሚነት ለማሻሻል አቅማቸውን አሟጥጠው መጠቀም ይኖርባቸዋል። በተለይም የባሕር በርን የተመለከተ ገዘፍ ያለ ጉዳይ ሲሆን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኃላፊነታቸው የበዛ ስለመሆኑ ያነሳሉ፡፡

አቶ መሐመድ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዕድገትን ለማስፈንና የጋራ ጉዳዮችን ለማጉላት በሀገረ-መንግስት ግንባታ ላይ ምሁራን የአንበሳውን ድርሻ ሊወስዱ እንደሚገባ ገልጸው፣ ሃሳቦችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማቅረብ ኢትዮጵያን ወክለው መሞገት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ኢትዮጵያ መውጫ ኮሪደር ያስፈልጋታልና ጉዳዩ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የቤት ስራ ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይም ምሁራን በዚህ ረገድ ኃላፊነታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በቅድሚያ ትውልዱ ስለባሕር በር ሲነሳ መሽኮርመም ማቆም ይኖርበታል፡፡ ሲቀጥልም ኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይን ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ እድገትና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ ቆማ ተጠቃሚነቷን እንድታረጋግጥ በተለይም ምሁራን ሌት ተቀን መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ቀርቦ የኢትዮጵያን እውነት ማስረዳት፣ ትውልዱን ማስተማር፣ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን መስራት፣ ልዩ ልዩ ጥናቶችን በማካሄድ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ማመላከት ይገባቸዋል። በዚህም በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ሁኔታ መፍጠር ይችላሉ፡፡

አያይዘውም የባሕር በር ጥያቄን በሰላምና በሕግ አግባብ መጠየቅ መብትም አስፈላጊም መሆኑን ጠቅሰው፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለዚህ አጀንዳ እውን መሆን ሲጨነቅና አስተዋጽኦ ሲያበረክት ስለራሱ ህይወት እየተጨነቀና አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ሊረዳ እንደሚገባውም አስረድተዋል፡፡

ይህ ማለት የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ሲያገኝ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኑሮ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚፈጥረው አዎንታዊ ተጽዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ በመሆኑም ከምሁራን በተጨማሪ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የስነ ጥበብ ሰዎች፣ ሙዚቀኞች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ባለ ሀብቶችና ፓለቲከኞች ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ አክለዋል፡፡

እዚህ ጋር አሜሪካዊው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተመራማሪ ላውረንስ ፍሪማን (ፕ/ር) አስተያየት እናስከትል፡፡ ፕሮፌሰሩ እንዳሉት፣ “አንዳንድ አካላት የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ አድርገው እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ እውነታው ግን የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ፍትሐዊና የቀጣናውን ሀገራት በኢኮኖሚ የሚያስተሳስር ጠቃሚ አካሄድ ነው። የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትም ይህንን ከግምት ማስገባት ያስፈልጋቸዋል” ሲሉ ተናግሯል።

የሰላም ጠላቶች የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄን ግጭት ለመፍጠር እየሞከሩበት ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ በኩል በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ቀጣናዊ ትስስር በማጠናከር የባሕር በርን ማግኘት እንጂ ጦርነት እንደሌለ መግለጻቸውም የሚታወስ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከትናንት በስቲያው ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳብራሩት የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ሌሎች ሀገራትም ትክክል መሆኑን አምነው ተቀብለውታል።

የባሕር በር ጥያቄ እንዳንጠይቅ በኃይል የሚያስቆመን አካል እንደሌለ አስምሬ ማለፍ እፈልጋለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒትሩ፣ ከ120 ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተዘግቶ መኖር ስለሌለበት ብልፅግና ኖረም አልኖረ የባሕር በር ጥያቄ የኢትዮጵያ የህልውና ጥያቄ ሆኖ ይቀጥላል ሲሉም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉም “ብልጽግና ኖረ አልኖረ፣ ምክር ቤቱ ኖረ አልኖረ፣ መለወጥ እና ከድህነት መውጣት የሚፈልግ ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፉ ተሰምሮለት እስር ቤት ሊቀመጥ አይችልም” ነው ያሉት፡፡ “ሰላም ወዳድ ነኝ የሚል ማንኛውም አካል ከወንድሞቻችን ጋር አነጋግሮን በህግ አግባብ የኢትዮጵያ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን”ም ብለዋል፡፡ የባሕር በር ሕልም ብቻ አለመሆኑንም ተናግረው ለኢትዮጵያ ሰላም እና ልማት የሚጓጉ ሰዎች ለሰላም እና ለውይይት እንዲዘጋጁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአፍሪካ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ከሚኖረው አጠቃላይ ህዝብ አንድ ሶስተኛው የሚገኘው በኢትዮጵያ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በቀጣይ በአካባቢው ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ቀላል ባለመሆኑ ኢትዮጵያን ያካተተ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሥራት ምንም ምርጫ የሌለው ጉዳይ ያደርገዋል የሚሉት ደግሞ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ አቶ መሐመድ በሽር ናቸው፡፡

የባሕር በር ጉዳይ የጥቂት ቡድኖች፣ የግለሰቦች ወይም የፓርቲዎች ጥያቄ አለመሆኑን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ አሳሳች ፕሮፓጋንዳን ከመስማትና ከማሰራጨት ሊቆጠብ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ አቶ መሐመድ፡፡  የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያውያን በብዙ ነገር ላይ ውጤት አምጥተናል። ለሀገራዊ ልማት በጋራ ቆመናል፤ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በአብሮነት ገድበናል። በባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይስ እንዴት በጋር መቆም ሊያቅተን ይችላል የሚለው ደግሞ ወሳኙ ጥያቄ ሆኗል፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review