AMN – መጋቢት 3/2017 ዓ.ም
የክህሎት ክፍተትን ለመሙላት ያለመ የባለድርሻዎች የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) የክህሎት ልማት ሥራ በመንግስት ብቻ የሚሰራ ሳይሆን በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ጭምር ነው ብለዋል።
ይሁንና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ባለመገኘቱ መንግስት የክህሎት ልማት ዘርፍን ሪፎርም በማድረግ ተሳትፎአቸውን ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የመድረኩ ዋና ዓላማም ባለድርሻዎች የሥራ ገበያ ፍላጎትን በመለየት በአጫጭር ሥልጠናዎች ዜጎችን ብቁና ተወዳዳሪ ማድረግ እንዲችሉ መሆኑን ተናግረዋል።
የዲጂታሉ ዓለም ሰዎች በአጫጭር ሥልጠናዎች ህይወታቸውን የሚቀይሩበት በመሆኑ መንግስትም ይህን ታሳቢ ያደረገ ሥራ እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡

የክህሎት ክፍተትን ለመሙላት ለመጀመሪያ ጊዜ በግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ደረጃ ወደ ሥራ እንደሚገባ ገልፀው፣ በቀጣይ በሌሎችም ዘርፎች ላይ የክህሎት ልማት ላይ ከግሉ ዘርፍ ጋር እንደሚሰራ አብራርተዋል።
ይህም የኢንዱስትሪ ምርታማነት እና ተወዳዳሪትን የሚያሳድግ፣ የሥራ ገበያውን ብቁ የሰው ሀይል ፍላጎት እና አቅርቦትን የሚያስተሳስር፣ ለዜጎች ከፍተኛ የሥራ እድል የሚፈጥር እና የመንግስት እና የግል አጋርነትን እደሚያጠናክር ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እና የክህሎት ልማት ካውንስል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ሞገስ በበኩላቸው፣ የግሉ ዘርፍ ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን ክህሎት በሰው ሀይል ረገድ በማበርከት የሚጠበቅበትን እንደሚወጣ ተናግረዋል።
በዓለም ደረጃ ተቋማት ውጤታማ የሆኑት የሰራተኞቻቸውን ክህሎት አሳድገው በተገቢው መጠቀም በመቻላቸው መሆኑን አንስተዋል።
ወቅቱ የግሎባላይዜሽን በመሆኑ ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት እንደሚጠይቅም አንስተዋል።
ተወዳዳሪነትን ለመጨመር ደግሞ የሰው ሀይል እና ቴክኖሎጂ ወሳኝነት ያላቸው ሲሆን፣ የበቃ የሰው ሀይል 60 በመቶ፣ ቴክኖሎጂ 20 በመቶ፣ ፋይናንስ፣ መሰረተ ልማት እና ሎሎች ደግሞ 20 በመቶ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክቱ በመድረኩ ተብራርቷል።
በመድረኩ የሚዲያ አካላትን ያሳተፈ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
የክህሎት ልማትን ለማሳደግ ግንዛቤ በመፍጠር እና የግሉን ዘርፍ በማበረታታት ሚዲያው የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ ቀርቧል፡፡
በማሬ ቃጦ