ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለማስመረቅ እና ሪባን በጋራ ለመቁረጥ ህብረተሰቡ የድጋፍ ተሳትፎውን ሊያጠናክር እንደሚገባ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር ጥሪ አቀረቡ፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከፍፃሜ ለማድረስ ህብረተሰቡ እስከ አሁን እያደረገ ያለው ድጋፍ ይበል የሚያሰኝ መሆኑንም ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ገልጸዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ግንባታ 98.66 በመቶ መጠናቀቁን የገለጹት ወይዘሮ ፍቅርተ፣ የኮርቻ ግድብ እና ዋናው ግድብ ሙሉ በሙሉ ተሰርተው መጠናቀቃቸውን አመላክተዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ በገንዘብ እና በዓይነት ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን በማንሳት፣ በባንክ መረጃ መሰረት በቦንድ እና በልገሳ የተገኘው ገቢም 23.2 ቢሊየን ብር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይህ ገንዘብ ኢትዮጵያውያን ከህፃን እስከ አዋቂ በ8100 ኤ ከአንድ ብር ጀምሮ በማዋጣት እና ከ25 ብር ጀምሮ ቦንድ በመግዛት፣ በውጭ ሀገር የሚኖሩም በኦንላየን በተለያዩ መተግበሪያዎች ድጋፍ ያደረጉበት እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት 14 ዓመታት የህብረተሰቡ ድጋፍ አለመቋረጡን ያመላከቱት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ፣ አሁንም ግድቡን ለማስመረቅ እና ሪባን በጋራ ለመቁረጥ ህብረተሰቡ የድጋፍ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በታምራት ቢሻው