የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ 5ኛ የሆነውን የካንሰር ህክምና መስጫ ማእከልን ጨምሮ ከአራት ቢሊየን ብር በላይ ያስገነባቸውን ሃያ ሁለት የተለያዩ ፕሮጀክትቶችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል::
ፕሬዚዳንቱ አንጋፋው ዩኒቨርሲቲ እና ለአንድ ምዕተ አመት የህክምና የሰባዊ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለሰሜኑ የሃገሪቱ ህዝብ የመዳንና የመጠገን ህያው ምልክት ነው ብለዋል፡፡
ስመጥር ባለሙያዎችን እያፈራ የሚገኘው ሆስፒታሉ ከጎንደር ህዝብ ህይወት እና ኑሮ ጋር የተሳሰረ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከታሪካዊነቱ ባሻገር ከተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በዩኒቨርስቲው የሚመደቡ ተማሪዎችን ከከተማው ነዋሪ ጋር በማስተሳሰር ‘የቃል ኪዳን ቤተሰብ’ በሚል መርህ ለሌሎች ተቋማት በተሞክሮ ሊወሰድ የሚችል አርአያነት ያለው ተግባር እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የኢትትዮጵያን እና የአካባቢውን ክብር የሚመጥን ምርምርና ባለሞያ የማፍራት ጥረቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አደራ ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ የዩኒቨርስቲውን 70ኛ ዓመት እና የማስተማሪያ ሆስፒታሉን መቶኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ነው የተመረቁት::

ከፕሮጀክቶች መካከል በሀገሪቱ 5ኛ በአማራ ክልል ደግሞ የመጀመሪያ የሆነው እና በጤና አገልግሎቱ ስመጥር በሆነው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይድ ሆስፒታል ግቢ የተገነባው የካንሰር ህክምና መስጫ ማእከል ይገኝበታል፡፡
የማእከሉ መገንባትና አገልግሎት መስጠት መጀመሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ህክምናውን ለማግኘት ከዚህ ቀደም አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ሌሎች የህክምና ማእከል መሄድ ይጠይቅ የነበረውን በማስቀረት በአካባቢያቸው ህክምና እንዲያገኙ አስቻይ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን ተናግረዋል። ማእከሉ ከአካባቢው ነዋሪዎች አለፍ ሲልም ከሌሎች አከባቢዎች ለሚመጡ ህሙማንም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የተመረቁት ፕሮጀክቶች የሰው ሰራሽ እግር ማምረቻ ማእከል፣ የኦክስጅን ማምረቻ ፣ የቅድመ ህክምና የላብራቶሪ ህንፃ ፣ የህፃናትና የአዋቂዎች ህክምና ማእከል፣ የውስጥ ደዌና ፅኑኑ ህሙማን ማእከል፣ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ፣ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ማእከሎች ይገኙበታል፡፡
በፕሮጀክቶች ምረቃ መርሐ-ግብር ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባን ጨምሮ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጨምሮ ለፕሮጀክቱ መሳካት አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት እውቅና ተሰጥታል፡፡
በሸዋዬ ከፍያለው