የጠቅላይ ሚኒስትሩና የንግዱ ማህበረሰብ ውይይት አንድምታ

You are currently viewing የጠቅላይ ሚኒስትሩና የንግዱ ማህበረሰብ ውይይት አንድምታ

እንዲህ አይነት ውይይቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ምሁራን ገልጸዋል

ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ የገንዘብ  ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የፌዴራል መንግስት የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 1 ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ በገቢ ረገድም የውጭ እርዳታን ጨምሮ 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።

ከሚሰበሰበው ገቢ ውስጥ ወደ 1 ነጥብ 1 ትሪሊዮን ብር የሚሆነው ወይም 73 በመቶው ከታክስ ገቢ የሚሰበሰብ ሲሆን 129 ቢሊዮን ብር ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች፣ 236 ቢሊዮን ከልማት አጋሮች እንዲሁም 47 ከፕሮጀክቶች እርዳታ የሚሰበሰብ ነው፡፡

አብዛኛውን የበጀት ወጪ ከሀገር ውስጥ በታክስ ለመሸፈን ሲታቀድ፣ ለዕቅዱ መሳካት የገቢ አሰባሰብ አቅምን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ከፍ ያለውን ታክስ በመክፈል ደግሞ የንግዱ ማህበረሰብ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይህ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው ማህበረሰብ ምርት በማምረት እና አገልግሎት በመስጠት ከሚያገኘው ገቢ ነው ታክስ በመክፈል ለሀገር ልማት ከፍተኛ ሚና የሚጫወተው፡፡ በቅርብ ዓመታት እንደ ሀገር እየተመዘገበ ባለው የኢኮኖሚ እድገትና ለውጥም አሻራው ጉልህ ነው፡፡

የንግዱ ማህበረሰብ ውጤታማ ሆኖ ከታክስ የሚጠበቀውን ገቢ ማግኘት ይቻል ዘንድ ምቹ የቢዝነስ ከባቢያዊ ሁኔታዎች መፈጠርና ፈጣንና ቀልጣፋ መንግስታዊ አገልግሎት ማቅረብን ይጠይቃል፡፡ ከሰሞኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከንግድ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል። መድረኩ የንግድ ማህበረሰብ አባላት በሀገሪቱ እየተከናወኑ ባሉ የልማት እንቅስቃሴዎች የተገኙ ውጤቶችና እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች ዙሪያ የተለያዩ ሀሳቦችን ያነሱበትና መንግስትም ያሉ ችግሮችን  በጋራ ለመፍታት እንደሚሰራ ያረጋገጠበት ነው፡፡

በኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር ከፍተኛ ተመራማሪ ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ፣ መንግስት የንግዱ ማህበረሰብ ችግሮችን ለመፍታት በቅርበት በመገናኘት የሚያደርጋቸው ውይይቶች በ2018 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ የታቀደን ገቢ ለማሳካት ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።

በ2018 ዓ.ም የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀቱ ለመሰብሰብ የተያዘው የገቢ ዕቅድ ከዚህ ቀደም ከነበረው እያደገ የመጣና ከፍ ያለ ነው፡፡ በ2016 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት 512 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ነበር የሰበሰበው፡፡ በ2017 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ውስጥ 653 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

በመሰረቱ ለአንድ ሀገር ገቢ ዋነኛ መሰረት መሆን ያለበት የሀገሩ ዜጋ ነው። የውጭ ብድርና እርዳታ በብዙ ሀገሮች እንደተጨማሪ እንጂ በዋና በጀት ውስጥ አይያዙም የሚሉት ተመራማሪው ሞላ (ዶ/ር) በ2018 በጀት ዓመት ሊሰበሰብ የታቀደው ገቢ ባለፈው ዓመት ከተሰበሰበው ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ ነው፡፡ ለእቅዱ መሳካት የባለድርሻ አካላት ርብርብ ወሳኝነት አለው፡፡ የታክስ መሰረቱን ማስፋት፣ ያለውንም በወቅቱና በአግባቡ ለመሰብሰብ ያላሳለሰ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ የታቀደውን ታክስ መሰብሰብ ካልተቻለ በጀቱ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳረፍ የተያዙ የልማት ዕቅዶች እንዲደናቀፉ ያደርጋል፡፡

በአንድ ሀገር ልማት ውስጥ ዋነኛ የልማት አጋር ተደርገው የሚወሰዱት መንግስት፣ ባለሀብቱና ህዝቡ ናቸው፡፡ መንግስት ቁልፍ የልማት አጋር ከሆነው የንግድ ማህበረሰብ ጋር ተቀራርቦ በመስራት ያሉበትን ችግር መፍታትና ለሀገር የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ መስራት ይገባል፡፡ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ያደረጉት ዓይነት ውይይቶችም መደበኛ በሆነ መልኩ መቀጠል አለባቸው፡፡

ባለሀብቱም መሰረተ ልማቶች ሊሞሉለትና የተሻለ አገልግሎት ሊያገኝ የሚችለው በሚከፍለው ግብር መሆኑን በመገንዘብ ታክስ በመክፈል የዜግነት ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል። መንግስት ገቢን ፈጣን፣ ቀልጣፋና ግልፅነትን ተላብሶ መሰብሰብ እንዳለበትም ከፍተኛ ተመራማሪው ሞላ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገ ውይይት፣ የንግድ ማህበረሰብ አባላት የሚከፍሉት ገንዘብ ህዝብና ሀገርን በሚጠቅሙ ልማቶች እየዋለ እንደሚገኝ በመግለጽ ለመንግስት ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የአምራች ነጋዴዎችን ችግሮች ለመፍታት የተሰጠው ትኩረት፣ የንግድ ፈቃድ ከማውጣት ጀምሮ አገልግሎቶችን በቀላሉ ማግኘት እንዲቻል እየተደረገ ያለው ድጋፍ የሚደነቅ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል ስራቸውን ለማከናወን ማነቆ የሆኑባቸው የተለያዩ ችግሮች እንዳሉ አንስተዋል፡፡ ህገ ወጥ ንግድ፣ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በተለይ በክፍለ ሀገር አካባቢ፣ ለአምራች ኢንዱስትሪው የሚቀርበው ፋይናንስ አቅርቦት በቂ አለመሆን፣ የመንግስት አገልግሎት ብቁ አለመሆንና ብልሹ አሰራር ከጠቀሷቸው መካከል ይገኙበታል፡፡ በየቦታው የሚዘረጉ ህገ ወጥ ኬላዎችና አላስፈላጊ ቀረጥ ችግር እንደፈጠረባቸው እንዲሁም በሀገሪቱ ዘላቂነት ያለው ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በንግዱ ማህበረሰብ የተነሱ ችግሮች የዕቅድ አካል ተደርገው መፍትሔ ለማበጀት እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡ ህገ ወጥነትን በተመለከተም “ማታለል” እንደ “ብልጠት” ተደርጎ እየተወሰደ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግስት ማግኘት ያለበትን ገቢ ሳያገኝ ዕቃዎች በህገ ወጥ መንገድ (በኮንትሮባንድ) ይወጣሉ፤ ይገባሉ፡፡ ለምሳሌ፡- በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ዋጋ ከጎረቤት ሀገራት አኳያ ሲታይ ርካሽ ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ ተገዝቶ ድጎማ ተደርጎበት የሚቀርበው ነዳጅ ሆን ተብሎ ከሀገር እየወጣ በጎረቤት ሀገራት ይሸጣል፡፡ ከእኛ ይልቅ ጎረቤት ሀገራት እየተጠቀሙበት ስለሆነ በመሀል የንግዱ ማህበረሰብ ሊጎዳ ይችላል፡፡ ከዚህ አኳያ “ነዳጅ ከሀገር እንዳይወጣ የምትጠብቁና የምትጠቀሙ መሆን አለባችሁ” ብለዋል። ከነዳጅ ጋር ተያይዞ የተነሱ ጉዳዮች በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኩል መፍትሔ ይሰጠዋል ነው ያሉት፡፡

ሌላው ፋይናንስ በምንፈልገው መጠን እያገኘን አይደለም የሚል ጥያቄ ከንግዱ ማህበረሰብ ተነስቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፣ ከሀገራዊ ለውጡ በፊትና በለውጡ ማግስት አካባቢ 80 በመቶ አካባቢ የሚሆነውን የባንክ ብድር የሚወስደው መንግስት ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የግሉ ዘርፍ የሚፈልገውን ብድር ሳያገኝ ቆይቷል። አሁን ላይ ግን እስከ 85 በመቶ ብድር ለግሉ ዘርፍ እየቀረበ ይገኛል፡፡ ይህም ሆኖ የሚቀርበው ብድር ካለው ፍላጎት አኳያ በቂ ስላልሆነ በተለይ ለኢንዱስትሪዎች የሚቀርበውን እንፈትሸዋለን፡፡ የባንኩ ዘርፍ ለውጭ ገበያ ክፍት እንዲሆን በመደረጉም በውድድር የተሻለ አገልግሎት ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡

ከፍተኛ ተመራማሪው ሞላ (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት፣ ያለ ፋይናንስ አቅርቦት ኢንቨስትመንትን ማሳደግ አይቻልም፡፡ ፋይናንስ የቢዝነስ እንቅስቃሴን ለማሳደግ ዋነኛ ግብአት በመሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ ምን እንደሚፈልግ በመረዳት መንግስት የተሻለ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር መስራት ይጠበቅበታል፡፡

በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር እንዳለ የተነሳው ሀሳብ ትክክለኛ እንደሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለዚህም በመፍትሔነት እየተወሰደ ያለው አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማስደገፍ መስጠት ነው። ይህም ውጤታማነትን በማሳደግና ሌብነትን በመቀነስ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ሌብነትን ለመቀነስ የንግዱ ማህበረሰብም ከሌባ ጋር ባለመተባበር፣ እጁን በመሰብሰብና ብልሹዎችን በማጋለጥ የራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ከፍተኛ ተመራማሪው ሞላ (ዶ/ር) እንዲሁ የመንግስት አገልግሎትን ቀልጣፋና ግልፅነትን የተላበሰ ማድረግ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ያነሳሉ፡፡ የተንዛዛና ብልሹ የሆነ አገልግሎት የሀገር ውስጥን ብቻ ሳይሆን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በሚፈለገው መጠን እንዳይመጣ ያደርጋል፡፡ የታቀደውን ገቢ ለማሳካት በተለይ በገቢ ሰብሳቢ ተቋማት ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ፈጣን አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት መዘርጋት ይገባል፡፡ “ግብር እየከፈልን የምንጉላላ ከሆነ ለምን እንከፍላለን” የሚል ቅሬታ ስለሚፈጠር የአገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል ለነገ የማይባል የቤት ስራ መሆን ይኖርበታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥም ባለሀብቱ ከሰላማዊ መንገድ ውጪ የሚንቀሳቀሱትን በመምከርና የሰላምን መንገድ እንዲመርጡ ጥረት በማድረግ የራሱን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል። መንግስት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሩ ክፍት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ህገ ወጥ ኬላዎች ጋር በተያያዘም የፍተሻ ኬላዎች የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ አስፈላጊ መሆናቸውን አንስተው፣ ነገር ግን “ለኮቴ” እየተባሉ የሚጠየቁ አላስፈላጊ ክፍያዎችን ለማስቀረት እንደሚሰራ አንስተዋል፡፡

አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ለልማት ቁልፍ መሰረት መሆኑን ያነሱት ሞላ (ዶ/ር)፣ አለመረጋጋት፣ በየቦታው ማን እንደዘረጋቸው የማይታወቁ ኬላዎችና ያለአስፈላጊ ክፍያዎች የንግዱ ማህበረሰብ እንዲማረር የሚያደርጉ በመሆናቸው ከክልሎች ጋር በመቀናጀት መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በጥቅሉ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረገው ውይይት የንግዱ ማህበረሰብ መወጣት ያለበትን ኃላፊነቶች፣ መንግስትም እንደ አገልግሎት አቅራቢ ሊፈታቸው የሚገባው ችግሮች የተነሱበት ነው፡፡ መንግስት በመደበኛነት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ውይይት በማድረግ አንገብጋቢ ለሆኑ ችግሮች መፍትሔ መስጠት ላይ ርብርብ ማድረግ አለበት። ይህን ማድረግ ሲቻል ነው ሊሰበሰብ የታቀደውን ገቢ ማሳካት የሚቻለው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የ2018 ረቂቅ በጀት ከታክስ የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳካት አዳዲስ የታክስ ፖሊሲዎችን በስራ ላይ ለማዋልና በስራ ላይ ያሉትን ማሻሻያዎች በተጠናከረ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ በስራ ላይ ያለውን የገቢ ግብር በመፈተሽ ለማሻሻል ታቅዷል፡፡ ለዚህም ጥናት ተደርጎ የህግ ማዕቀፉ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም ዘመናዊና የተሟላ የኤክሳይዝ ታክስ አስተዳደርን ስራ ላይ ለማዋል ዘመናዊ የቴምብር ስርዓት ለመዘርጋት የተጀመረው ስራ ተጠናቅቆ በመጪው ዓመት ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡   

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review