AMN-ጥር 10/2017 ዓ.ም
“የጥምቀት በዓልን በጽዱ አዲስ አበባ! “
በሚል መሪ ሀሳብ የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ማሪያም የታቦታት ማደሪያ የጽዳት መርሐግብር ተካሂዷል፡፡
በመርሐግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የጽዳት አምባሳደሮች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም ሀይሌ በክፍለ ከተማው ለበዓሉ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርና በዓሉ በስኬት እንዲከበር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
የጥምቀት በዓል የሚከበርበትን ቦታ በአብሮነት በማፅዳት የተሳተፉትን የሁሉም ሀይማኖት ተወካዮች እና የህብረተሰብ ክፍል አመስግነዋል።
የጥምቀት በዓል ፍቅርና አብሮነትን የሚያስተምር ነውም ብለዋል።

በፅዳት ዘመቻው ህብረተሰቡ አንድነቱንና ትብብሩን ያሳየበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በፅዳት ዘመቻው የተሳተፉ የተለያዩ ዕምነት ተከታይ ግለሰቦች በበኩላቸው በዓሉ የሁላችን ደስታ ነው ያሉ ሲሆን በጽዳት ዘመቻው ላይ አክብሮታቸውን ና አንድነታቸውን ለመግለጽ መገኘታቸውን ገልፀዋል።
በቦሌ ክፍለ ከተማ የማሪያም ቤተ ክርስቲያን ተወካይ መጋቤ ሀይማኖት አክሊሉ የጥምቀት በዓል ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያሳየውን ፍቅርና ትህትና ያሳየበት ነው ብለዋል።
ሀገራችን የምትታወቅበት ፍቅር፣ አብሮነት፣ አንድነት፣ ወንድማማችነት እና መቻቻልን ለመግለፅ በፅዳት ዘመቻው የተለያዩ እምነት ተከታዮችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መገኘታቸውን ገልፀው ትብብሩን የሚያጠናክሩ እሴቶች ናቸው ብለዋል።
በመሐመድኑር አሊ