የጥበብ መቀነት በሰው፣ ሀገርና ማህበረሰብ ዙሪያ

ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች የማህበረሰቡን ትክክለኛ መልክና ገጽታውን የሚያሳዩ መስታወት ናቸው። የማህበረሰቡን እሴቶች፣ በቅጡ ያልታዩ ማህበራዊ መስተጋብሮችና ትኩረት ያልተቸራቸው ጉዳዮች በስራዎቻቸው አጉልተው ያሳያሉ፡፡ እንዲሁም የማህበረሰቡን ትክክለኛ ገጽታና ክፍተቶቹን በፈጠራ ስራዎቻቸው አማካኝነት እንደ መስታወት ጥርት አድርገው ያስመለክታሉ፡፡ ለዚህ ነው እውነተኛ ከያኒ የማህበረሰቡ መስታወት ነው የሚባለው፡፡ በዚህ የኪነ ጥበብ እሳቤ አውድ ውስጥ የተቃኘው የወጣቱ ገጣሚ ዲበኩሉ ጌታ ‘ሰው እስካለ ድረስ’ የተሰኘው የግጥም መጽሐፍ ላይ አጭር ዳሰሳ እንደሚከተለው አድርገናል፡፡

በያዝነው ዓመት ለህትመት የበቃው የገጣሚ ዲበኩሉ ሁለተኛ የግጥም መጽሐፍ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻ ድረስ፣ ‘ሰው እስካለ ድረስ’ በማለት ስለሰው ክብር የሚያትቱ ሃሳቦች ጎልተው መጽሐፉ ውስጥ ይሰማሉ፡፡ የሰው ልጆችን ሕይወት በጥልቀት ያጠይቃሉ፡፡ ግጥሞቹ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ተመርኩዞ ማህበረሰብና ሀገርን ያስቃኛሉ፡፡

በ‘ሰው እስካለ ድረስ’ መጽሐፍ ውስጥ የሰው ልጆችን ክብር ማጉላት ብቻ ሳይሆን፣ ህይወታቸውንም በጥልቀት ይፈትሻል፣ ይሄሳልም፡፡ “ሕይወት” በተሰኘው ግጥሙም “ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም” የሚለው ሀገርኛ ብሂልን አጉልተው የሚያሳዩ ስንኞች እንዲህ አስፍሯል፤

…የለም ሙሉ ስሕተት ከቶም ፍጹም ስኬት

የለም መርጦ መሆን ዘሎ ማቀፍ ቅጽበት

የለም በተናጠል ዕንባ ያለ ደስታ

የለም ያለ ጥምረት ተስፋ አልባ ትዝታ…

በ‘ሰው እስካለ ድረስ’ ውስጥ የተካተቱት ግጥሞች  ህይወትን ይሄሳሉ፡፡ ገጣሚው ከኑረታችን ውስጥ ዥንጉርጉር ሰበዞችን እየመዘዘ የህይወትን ሌላኛው ገጿን በድፍረት ያሳዩናል፡፡ ገጣሚው ሕይወትን እንደ ቂጣ በሁለቱም ጎኗ እያገላበጠ ያጠይቃል፡፡ በልማድ የተስማማንባቸው ጉዳዮችን ይሞግታል። ከወል ዕውነታ ባሻገር ሌላ ዕውነት መኖሩን ጭምር ያሳየናል፡፡

ገጣሚው በዚህ መጽሐፉ የጋራ ጀግኖቻችንን አጉልቶ ለማሳየት ጥረት ያደርጋል፡፡ ብሔራዊ ጀግኖቻችንን የልዩነት አጥር አጥረን እንዳንገድባቸው ያሳስባል፡፡ ብሔራዊ ጀግኖቻችን የሁላችንም ጀግኖች ናቸው ሲል “ሰለሞን ዴሬሳ” በሚል ርዕስ፣ ታላቁን ባለቅኔ ሰለሞን ዴሬሳን መነሻ በማድረግ እንዲህ ይሞግተናል፡፡

…አለን እኮ ነቢይ ሰለሞን ጠቢቡ

ለምንድነው ታዲያ አምኖ መጠርጠሩ?

አዎ! ስለ‘ምንድን?

አንዱን ጋራ ከአንዱ-በሐረግ ማጠሩ

በጣም ደግሞ ለምን?

በሰው መሐል ሥጋ – ነፍስ መከፈሉ፡፡

ሌላው ገጣሚው ለየት ያሉ አተያዮችና ሃሳቦችን በዚህ የግጥም መድብሉ ውስጥ ያሳየናል፡፡ “አንድ አሮጌ መጽሐፍ” በተሰኘው ግጥሙ፣ የአሮጌ መጽሐፍ ውብ ጸዳል እንድናይ ያደርጋል፡፡ አሮጌ መጽሐፍ ውስጥ የተሰነዱ ውብ ሃሳቦችን ከፍቶ ያስነብበናል፡፡ አሮጌን መጽሐፍ ልክ እንደ አንድ አፍሪካዊ አዛውንት ታሪክ ሰናጅና ታሪክ ነጋሪ አድርጎ አጭቶታል፡፡

አሮጌ መጽሐፍ ለክፍለ ዘመን እልፎች ያነበቡት

ከጄ ገባ ዛሬ፤

ትውልድ አቆራርጦ-በዓለም እሽክርክሪት…

ይናገራል ገጹ ብዙ መነበቡን

የሕትመት ዓመቱም ይጠቁማል እሱን

በተለያየ ቀን በተለያየ ሰው በክብር ያረፈ

ብዙ ፊርማም ይዟል-ሰው ከጎን የጻፈ…

አሮጌ መጽሐፍ፣ ታሪኮች ያቀፈ

ብዙ አንጎል ደክሞበት፣ በእልፍ የተነበበ

የነኩትን ሁሉ፣ ወዝ እንደጠገበ

ዋጠኝ በሰመመን፣ ጊዜ እያሳሰበ…

ያሳስባል ብዙ…

አሮጌ መጽሐፍ፣ ሌላም መሰል ነገር!

ትውልድ እያሰሰ፣ እውነት ሚያዋርሰው፣ በጊዜ መነጽር፡፡

አሮጌ መጽሐፍ…

ገጣሚው እጅግ ደቃቅ የሚመስሉ ሃሳቦችን አግዝፎ በማሳየት ተክኖበታል፡፡ ከላይ የሰፈሩት የአሮጌ መጽሐፍ የግጥም ስንኞችም ይህንኑ ይመሰክራሉ፡፡

ከያኒ ለኪነትም ለህይወትም ስሱ መሆን አለበት፡፡ ፈረንጆች ™Aesthetic sensibility” ብለው ይጠሩታል፡፡ ከያኒው ይህን ስሱነት የሚያረጋግጠው አንድም ሕይወትን ሳይፈርጅ በመኖር ነው፡፡ አስቀድሞ ፍረጃ ግን የሕይወትን ጣዕም ያጎመዝዛል፡፡ የተባለውን ከመድገም ባለፈ ኪናዊ ውበትን ፈልቅቆ ማሳየት ትንሽ ያዳግታል፡፡ ታዲያ ከያኒው ለሕይወት ስሱ መሆን አለበት ሲባል ሕይወትን እስከነ ጉድፎቿ ውብ አድርጎ መከየን ማለት ነው፡፡

ዲበኩሉም በግጥሞቹ ውስጥ የህይወትን አምሳለ-ብዙ ገጾችን የውበት መጎናፀፊያ አልብሶ ያሳየናል፡፡ ይህን ለማድረግ ትልቅ አቅምና ድፍረት ይጠይቃል፡፡ ገጣሚው ግን የማይደፈሩ የሚመስሉ ቅጽሮችን ዘልቆ በመግባት የተገፉ ሃቆችን ወደ ማዕከል ያመጣቸዋል።

ደግሞስ የስንዴን ዘለላ ያለ እንክርዳድ እንዴት ማሰብ ይቻላል? አንድ ገበሬ ስንዴን ዘርቶ፣ የተትረፈረፈ ስንዴን ለማጨድ አስቀድሞ እንክርዳዱን ማጥፋት ከቶም አይቻለውም፡፡ የስንዴ ዘለላና እንክርዳድ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸውና፡፡ ህይወትም እንደዚያ ነች። ፍሬና አረም በህይወት ገጽ ላይ አብረው ይበቅላሉ፡፡ በሂደት ውስጥ ፍሬውን ከገለባው እየለዩ መኖር ነው የህይወት ውሉ፡፡ ገጣሚው “ከሕልሞችህ ጋራ” በተሰኘው ግጥሙ ይህንኑ ያሳየናል።

ከመታቀብ ልክነት

የመሞከር ስሕተት

ካልፈተሹት ምግባር

የመድፈሩ ውግዘት…

ባይሰምርም አትዘን

ብትወድቅ አትፀፀት፡፡

ገጣሚው መሳሳትም (ሳ ጠብቆ ይነበብ) የሕይወት አካል ነው ይለናል፡፡ አዎን መሳሳትም የሕይወታችን ሌላኛው ገጽ ነው፡፡ ገና ስንወለድ አንስቶ በመሳሳት ጭምር ነው እየተማርን የጎለመስነው። ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎችም ከእነዚህ ዥንጉርጉር የህይወት ሰበዞች እየተመዘዙ ሲከየኑ፣ ክየናው ህይወት ይኖረዋል፡፡ የጥበብ ስራዎችም ሰዋዊ ቃና ስለሚኖራቸው ለልብ ይቀርባሉ፡፡

 ሌላው ኪናዊ የፈጠራ ሥራዎች የአንድን ነገር ዕውነታን ወይም ስሁትነትን ለማረጋገጥና ለማጽናት አይደለም የሚከየኑት፡፡ ከዚያ ይልቅ ሕይወትን በአዲስ መንገድ እንድንረዳትና ዓለምን ከሌላ አውታር እንድንመለከታት ማስቻል ነው፡፡ ገጣሚው በዚህ የግጥም ስብስቡ ከደስታና ስቃያችን፣ ከሳቅና እንባችን ብዕሩን እየነከረ በሕይወት ሸራ ላይ ኑረታችንን ይስላል፡፡  ፈጣሪውን ሲሞግተው ቆይቶ፣ ተመልሶ “ትንሽ ዕድሜ” እንዲሰጠው ይማጸናል፡፡

ስለ ኪነት ፍቅር ስለ ጥበብ ቃና

ስለ’ሱም ለማውጋት ከማላዮች ጋራ

ትንሽ ዓመት ጨምር አባት ሆይ አደራ፤

ስለ አርምሞም ሲባል ስለጥልቅ ጥሞና

ስለ’ራስን ማኩረፍ ተጣልቶ በፀና

ትንሽ ፍቀድ ወሽመጥ ትንሽ እንደገና

ከራስ መከፋፈል ጊዜ ይሻልና…

ከዘወትራዊ የሕይወት መብከንከን ታቅቦ፣ ስለ ኪነት ማውጋት እንዴት ያስደስታል? ነገር ግን ዘመኑ ቅጽበታዊነት ላይ በመመስረቱ የፅሞናን ጊዜ ነጥቆናል፡፡ በውበት ለመማለል፣ በጽሞና ለመቆዘምና ራስን በሚገባ ለመመርመር ገጣሚው እንዳለው ጊዜ ይሻል፡፡ ከትርምሱ መራቅ፣ ከውጥንቅጡ መገለልን ይሻል፡፡

ከጊዜ መሐል ገጽ ከዕድሜ ሰሌዳው

ተጽፏል አንድ ቃል ገላጭ የሚያነበው፤

ይላል፡-

ሰው በሰርክ ተምጦ ከጣር ይወለዳል

ጊዜ አዘቦት አያውቅ ኹለ’ዜ ይጓዛል፤

በዚህ ኹሉ መሐል-ሁሉም ሲያይ ይጠፋል፤

ቢሉም፤

ተስፋ የጋራ ውርስ-ትውልድ ያዳርሳል፤

ትዝታም ኹለንታን ጣጥሶት ላይሻር-በኹሉ ይነግሳል፡፡

“ከጊዜ መሐል ገጽ- የተነበበ አንቀጽ” ከተሰኘው ግጥሙ የተወሰዱ ስንኞች ናቸው፡፡ ይህ ግጥም ብዙ ያስቆዝማል፡፡ ስለ ጊዜ እንድናስብ ይተነኩሰናል፡፡ ጊዜ ግን ምንድነው? ከምዕራቡ ዓለም ተነስቶ ሁለንተናዊ ለመሆን እንደተቃረበው ግብ-ተኮር (linear) ወይም ጊዜ ከትናንት ተነስቶ፣ በዛሬ አድርጎ፣ ወደ ነገ የሚተምም ነው? ወይስ እንደ አፍሪካዊ ነባር ባህል ጊዜ ተፈራራቂ (circular) ነው፡፡ ክረምትን በበጋ፣ ምሽትን በቀን፣ ልጅነትን በእርጅና፣ ህይወትን በሞት እያፈራረቀ የሚተካ፡፡ ታዲያ በዚህ አፍሪካዊ የጊዜ እሳቤ መሰረት ሕይወት ውስጥ ቋሚ የሆነ ነገር የለም፤ ሁሉም ነገር የሚለዋወጥና እያየነው የሚያልፍ ወይም የሚጠፋ ነው። በሀገራችን ማህበራዊ ህይወት ውስጥ ይህንን የጊዜ እሳቤ ገናንና እምነት እንዳለው ይታወቃል፡፡

በዲበኩሉ ‘ሰው እስካለ ድረስ’ የግጥም ስብስብ ውስጥ ጊዜን የሚያጠይቁና የሚሞግቱ ግጥሞች አሉ፡፡ በእነዚህ ግጥሞች ገጣሚው የጊዜን ተለዋዋጭነትና አይጨበጤነት ላይ ደጋግሞ ያስባል። ይኸውም ሆኖ ግን ጊዜን በተመለከተ የተለያዩ አተያዮችን በግጥሞቹ ሊያሳየን ይሞክራል፡፡ ጊዜን ማዕከል አድርጎ የጻፋቸው እነዚህን ግጥሞች በአንድ ጎናቸው የጊዜን አይጨበጤነት ሲያትቱ በሌላ ገጻቸው ደግሞ ከጊዜ ተስፋን ይማፀናሉ፡፡

በ‘ሰው እስካለ ድረስ’ የግጥም ስብስብ ውስጥ የተካተቱት አንዳንድ ግጥሞች ራሳችንን እንድናይ መነሳሳትን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ በተለይ የመጨረሻ ዕውነት አድርገን የተቀበልናቸው ገናንና ተረኮችን ስለሚያጠይቁ፣ በልማድ የተቀበልናቸው ነገሮችን መለስ ብለን በጽሞና እንድናጤንና እንድንመረምራቸው የማድረግ አቅም አላቸው፡፡ 

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review