AMN – የካቲት 2/2017 ዓ.ም
በአዳማ ጨፌ አዳራሽ እየተካሄደ የሚገኘውን የጨፌ ኦሮሚያ 4ኛ ዓመት 6ኛ የስራ ዘመን 8 መደበኛ ጉባኤ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባኤ ሰዓዳ አብዱራህማን በንግግር ከፍተውታል።
አፈ-ጉባኤ ሰዓዳ አብዱራህማን መንግስት ለታጠቁ ሐይሎች ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ የሰላም መንገድን መርጠው ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመጡት አካላት ምስጋና አቅርበዋል ፡፡
ቀሪዎቹም የነሱን መንገድ እንዲከተሉም አፈ-ጉባኤዋ በጨፌው ስም ጥሪ አቅርበዋል ።
ባለፉት ጊዜያት ኢትዮጵያን የሚያሰባስብ እና አንድ የሚያደርግ የጋራ ትርክ ግንባታ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት መስራቱን ገልጸዋል።
ኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የክልሉን የስድስት ወራት እቅድ ክንውን ሪፖርት አቅርበዋል።
በሪፖርቱም ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች ጋር የተደረገው የሰላም ስምምነት እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ከፍተኛ ስኬት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የሰላም አማራጩን የተከተሉትን የሰራዊቱ አመራሮችና አባለት እንኳን ደህና መጣችሁ ያሉት ፕሬዝደንቱ ፣ ሌሎች አካላትም በተመሳሳይ የሰላም መንገዱን እንዲመርጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፉት 6 ወራት እንደ ክልል ከውስጥ እና ከውጭ የገጠሙንን የጸጥታ ችግር በመቋቋም በርካታ ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች ተገኝተዋልም ብለዋል።
በዳንኤል መላኩ