ትላንት የተመረቀው የካዛንቺስ ኮሪደር እና መልሶ ማልማት አንዱ አካል የሆነውን የሴቶች አደባባይ የሴቶችን አጠቃላይ ሚና እና በትውልድ ግንባታ ውስጥ ያላቸውን ትልቅ ድርሻ በሚያጎላ መንገድ ገንብን አስመርቀናል።
አደባባዩ ስያሜውን ካገኘ ቆየት ያለ ቢሆንም ፤ የሴቶችን ሚና ሊያሳይ የሚችል ምንም የተለየ መገለጫ ያልነበረው እና አካባቢው ለአይን ብዙም የማይመች የነበረ ሲሆን ፤ በካዛንቺስ መልሶ ማልማት ስራ ግን ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እንዲሁም በፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን ወሳኝ ሚና በሚገልፅ መልኩ ተገንብቷል።
የሃውልቱ ሀሳብ ሩቅ የምትመለከት እና በእጇ ሚዛን የያዘች ሴት ምስል ሲሆን ይህም ሃገራችን ኢትዮጵያን የምትወክል ናት። የቆመችበት ችቦ ደግሞ ድልን ያሳያል።
ሀውልቱን የከበበው የጽጌረዳ አበባ እንደ ስሟ ውብ አበባ ለማድረግ እየተጋን ያለነውን ከተማችን አዲስ አበባን እንዲወክል ተደርጎ የተሰራ ሲሆን በአበባው ላይ ከዝቅተኛ ስራ እስከ ትልቅ ሃላፊነት በተለይም በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ ዘርፎች እስከ መሪነት ድረስ ሴቶች ያላቸውን ሚና የሚያንፀባርቅ ነው።

ይህ ብቻ ሳይሆን በዙሪያው የሚታየው የሴቶች ምስል፣ ሴቶች የኢትዮጵያን ብዝሃነት፣ ማህበራዊ ትስስሮች እና ባህሎች በማንፀባረቅ በኩል ያላቸውን አይተኬ ሚና ያሳያል።
በአደባባዩ ግራ ቀኝ የሚታዩት ምስሎች የሃገራችንን ባንዲራ በዓለም መድረክ እያወለበለቡ ከፍ ያደረጉልንን የሴት አትሌቶቻችን ጉልህ ሚና እና የኢትዮጵያን ነፃነት በማስጠበቅ ውስጥ የኢትዮጵያ ሴት አርበኞች ያደረጉትን ተጋድሎ የሚዘክሩ ናቸው።
በሌላ በኩል በአደባባዩ ግራ እና ቀኝ የሚታዩት የእንዝርት እና እንጀራ ሲጋገር የሚያሳዩ ምስሎች የተለየ ትምህርት እና ስልጠና ሳኖራቸዉ እናቶቻችን ጥጥ አባዝተው፣ ፈትለው እና ወደ ልብስነት ቀይረው የሚያለብሱ እንዲሁም እንጀራ ጋግረዉ የሚመግቡ በተፈጥሮ የተቸራቸውን ጥበብ እና የላቀ መረዳትን የሚያመላክት ነው።
በሴቶች አደባባይ ዙሪያ 105 ሱቆችን የገነባን ሲሆን በነዚህ ሱቆች 90% የስራ እድል ያገኙት ከመፍረሱ በፊት እዛዉ ንግድ የነበራቸዉ ናቸው።

በተጨማሪም በአካባቢው ላይ ከተለያዩ አስቸጋሪ ህይወት ውስጥ አውጥተን፣ አሰልጥነን ለስራ ያበቃናቸው ከየነገዋ የተሃድሶና ክህሎት ማበልፅጊያ ማዕከል የተመረቁ ሴቶች የሚሰሩባቸው ፀጉር ቤት፣ ካፍቴሪያ፣ ሬስቶራንት፣ የልብስ ስፌት፣ ስጋ ቤት እንዲሁም የአረንጓዴ ልማት ስራዎቻችንን በመንከባከብ የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ የተደረጉ የሚሰሩባቸው ናቸው። ሌሎቹ አብዛኛዎቹ ሱቆች በአካባቢው ይነግዱ የነበሩና ስራቸውን እዚያው በተለመደው ስፍራ እንዲቀጥሉ የተደረጉ ነጋዴዎች የሚሰሩባቸው ናቸው።
ሴትን ማክበርና ማብቃት የስልጣኔ ማሳያ እና የሃገር ብልፅግና መሰረት በመሆኑ እጅ ለእጅ ተያይዘን ሁላችንም ይህንን ለማረጋገጥ እንስራ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ