AMN – ታኅሣሥ 12/2017 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት የመጡትን የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ተቀብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ በ2011 ዓ.ም በነበራቸው ጉብኝት ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የእድሳት ሥራ ድጋፍ እንደሚሰጡ አሳውቀው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡ በታደሰው ብሔራዊ ቤተመንግሥት ፕሬዝዳንቱን የተቀበሉ ሲሆን ቤተመንግሥቱንም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በሁለትዮሽ ውይይታቸው ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፈረንሳይ ለብዙ ዘመናት ተዘንግቶ ለቆየው የብሔራዊ ቤተመንግሥት እድሳት ላደረገችው የእድሳት ድጋፍ አመስግነዋል።
ፕሬዝዳንት ማክሮን በበኩላቸው አስደማሚውን የቤተመንግሥት እድሳት አድንቀው በአድዋ መታሰቢያ ግንባታ እንደታየው የኢትዮጵያን ታሪክ እና ባሕል ለማክበር የተደረገውን ጥረት ክብር ሰጥተዋል።
መሪዎቹ ሰፊ መጠነ ርዕይ ባላቸው የሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በኢንቬስትመንት፣ ባሕል እና ትምህርት ትብብር ለማጠናከር ተስማምተዋል።
የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በተመለከተም ረጅም ዘመን ለቆየው መሻት ዘላቂ መፍትሔ ለማስገኘት ሁለቱ ወገኖች በጋራ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለጻቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።

All reactions:
98Anbessa Tefera Biru and 97 others