የፌደራል መንግሥት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ለመተግበር በትኩረት እየሰራ ነው- ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

You are currently viewing የፌደራል መንግሥት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ለመተግበር በትኩረት እየሰራ ነው- ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

AMN – መጋቢት 5/2017 ዓ.ም

የፌደራል መንግሥት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ለመተግበር በትኩረት እየሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ማብራሪያ ተሰጥቷል።

በመድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትግበራ ውስንነቶች ቢኖሩበትም፣ የፌዴራል መንግሥት ሙሉ በሙሉ ለመተግበር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አንዱ ዓላማ ተኩስ ማቆም መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ መንግስት በትግራይ ክልል የተከሰተውን ወቅታዊ ሁኔታ በትኩረት እየተከታተለ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ገቢራዊ ለማድረግ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በትብብር እንሰራለን ብለዋል።

በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ፣ የሰላም እና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ በበኩላቸው በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ሁሉም ጥረት ማድረግ አለበት ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ችግሩን በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት በሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም መግለፃቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review