AMN – የካቲት 16/2017 ዓ.ም
የፌደራል ፖሊስ ከ21ሚሊየን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን መያዙን አስታውቋል፡፡
የኮንትሮባንድ እና ሌሎች የንግድ ማጭበርበር ወንጀሎች በሕጋዊ የንግድ እንቅስቃሴ፣ የሕዝብ ደህንነት እና በመንግሥት ገቢ እንዲሁም በሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቶች ላይ የሚያስከትሉትን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተጠናከረ የሕግ ማስከበር ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጿል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኮድ 3-15247 ኢት ተሽከርካሪ 21ሚሊየን 372 ሺህ 120 ብር የዋጋ ግምት ያላቸውን የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ጭኖ ሕጋዊ ለማስመሰል ባዘጋጀችው ሀሰተኛ ሰነዶች በማጭበርበር የደብረብርሃን አርሴማ ኬላ ለማለፍ ሲሞክር በኢትዮጵያ የፌዴራል ፖሊስ የሰሜን ምስራቅ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ሥር መዋል መቻላቸውን አስታውቋል።

አሽከርካሪውም በኮንቴነሩ ውስጥ ደብቆ ከጫናቸው ከበርካታ የሺሻ ዕቃዎች፣ ከተለያዩ ሲጃራዎች እና ቦንዳ ልባሽ ጨርቃ ጨርቆች ጋር በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።
ኮንትሮባንድን ከመቆጣጠር አንጻር እስከአሁን ለተገኘው ውጤት የሕዝቡ ተሳትፎ በጣም ከፍተኛ ነበር ያለው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ በቀጣይም ኅብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረቡን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።