የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማሳያዎች

You are currently viewing የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማሳያዎች

ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በመንግስት የሚሰሩ ማናቸውም የልማት ስራዎች፣ ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ ሲቻል ብቻ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  በቅርቡ እንደገለጹት፣ “ሀገራችን አድጋለች ማለት የሚቻለው ዜጎች ከዕድገቱ ምን ያህል ተጠቃሚ ሆኑ?” የሚለው ቁልፍ ሃሳብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይን እና ፕላን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦ፣ የአዲስ አበባን የከተማነት ደረጃ በተጨባጭ ሁኔታ ከለወጡ እና የፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ካሳደጉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በቀዳሚነት የሚጠቀስ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ እና በመከናወን ላይ የሚገኙ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች፣ የከተማዋን ዓለም አቀፋዊነት ደረጃ ከፍ ያደረጉ፣ የስማርት ሲቲ እና የአካታች ወይም ሁሉን አቀፍ መርህን የተከተሉ እና የዜጎችን የፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጡ ናቸው፡፡ 

በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፣ ለከተማ ዕድገት ቁልፍ የሆነውን የመንገድ መሰረተ ልማት ያሳደገ እና ያሻሻለ፣ የነዋሪውን ማህበረሰብ የአኗኗር ዘይቤ የቀየረ፣ ሕብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን አገልግሎቶች በቅርብ ርቀት የሚያገኝበትን ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን ፕሮፌሰሩ አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የኮሪደር ልማት ዋና እሳቤው ለልጆቻችን መልካም ሀገር እና ከተማን ጥሎ ማለፍ ነው፡፡ ስለዚህ  ከዚህ ቀደም የነበሩ ሰፈሮች የደቀቁ ከመሆናቸው የተነሳ ለኑሮ የማይመቹ እና አስቸጋሪ መሆናቸውን በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ አንስተዋል፡፡

ይሁን እንደጂ አሁን ላይ እንዚህ ሰፈሮች እየተቀየሩ ይገኛሉ፡፡ ለኑሮ ተስማሚ፣ ምቹና አረንጓዴ ለብሰው በመታየታቸው ለነዋሪዎችም ሆነ  ለተመልካች ሳቢ እየሆኑ መምጣት ችለዋል፡፡

እነዚህ የኮሪደር የልማት ስራዎች እየተሰሩ የሚገኙት በከተማ ብቻ ሣይሆን፣ በገጠሩ የሀገራችን ጭምር ሲሆን፣ ይህ የሚያሳየው አንዱ የበይ ተመልካች እንዳይሆን እና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህ እንዲተገበር ያለመ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መዲናዋን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ መሰራቱን ጠቁመው፣ በኮሪደር ልማት ሥራው ከመኖሪያ አካባቢያቸው ለተነሱ ዜጎችም ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ መከፈሉን አስታውሰዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ከ167 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች መተላለፋቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በኮርደር ልማቱ የተነሱ ዜጎች የተሻለ መሰረተ ልማት ወደ ተሟላላቸው አካባቢዎች መግባታቸውንም ገልጸዋል፡፡

 ይህም የህዝባችንን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጥንበት ስራ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ 

የኮሪደር ልማቱ ዋና አላማ ከተማችንን ለመኖር ምቹ ማድረግ፣ ማደስ፣ ገጽታዋን ማሻሻል እና ከልማቱ ማንም ወደ ኋላ ሳይቀር ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ  አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡

ከንቲባዋ፣ በአብዛኛው በአዲስ አበባ ከተማ አካባቢዎች ይኖር የነበረው ማህብረሰብ በብዛት ከቆሸሹና ካረጁ ነገሮች ጋር የተላመደ እንደነበረ አስታውሰው፣ የኮሪደር ልማቱ ማህበረሰቡን ከዚህ አኗኗር አላቆ ጽዱና ውብ አካባቢ መኖር፤ መነገድ፤ ለጤና የሚመች አካበቢ መፍጠር ያሥቻለ እና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄን በአግባቡ የመለሰ ስለመሆነ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት የለውጥ አመታት ከ35 ሺህ በላይ ቤቶች ተገንብተው ለዜጎች ማስተላለፍ መቻሉንም ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡

እንደ ከተማ እየተሰራ ያለው ስራ የኑሮ ጫናን ለማቃለል፣ አስተሳሰብን ለመቀየር፣ የተዛቡ ትርክቶቻችንን ለማስተካከል እና ሁሉም የሀገሩ ፍቅር ከፍ እንዲል ለማድረግ መሆኑን ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡

የለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የፍትሐዊ ተጠቃሚነት አንዱ ማሳያ ሲሆን ማዕከሉ በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያው ቀውስ ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ የተገነባ ማዕከል እንደሆነም ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን ሴቶችን ለማብቃት በከተማዋ የሚደረገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴና ልማት ሰሴቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግም ጭምር ታስቦ በልዩ በትኩረት የተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

 ማዕከሉ በዓመት እስከ 10 ሺህ ሴቶች በተለያዩ የሙያና የክህሎት ስልጠናዎችን በመስጠት በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የሚያግዝም ነው።

የሴቶች ታሃድሶ እና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል በተለያዩ ምክንያቶች ለማህበራዊ ቀውስ የተጋለጡ ሴቶችን ከመደገፍ ባለፈ፣ የተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚ በማድረግ እና ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር እንደሚረዳ ተመላክቷል፡፡

በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት እንደ ማሳያ አነሳን እንጂ ሌሎችም እንደ የትምህርት ቤት ምገባ፣ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን መመገብ የሚያስችል ከ21 በላይ የምገባ ማዕከላት፣ የዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤቶች፣በጉሌሌ እና በለሚ ኩራ የእንጀራ መጋገሪያ ፋብሪካዎች በርካታ ስራ አጥ ሴቶችን በማደረጃት የስራ ባለቤት ማድረግ እና ሌሎችም ባለፉት የለውጥ አመታት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጡ ተግባራት ናቸው፡፡

 በቶለሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review