የፕሪምየር ሊጉ ሽልማቶችና ሪከርዶች

AMN-ግንቦት 18/2017 ዓ.ም

የ2024/25 የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ትናንት ተጠናቋል፡፡ ከአመሻሽ ከ12 ሰዓት ጀምሮ በተመሳሳይ ሰዓት በተደረጉ 10 ጨዋታዎች የውድድር ዓመቱ ሊቨርፑልን አሸናፊ በማድረግ ተቋጭቷል፡፡

ሻምፒዮኑ ሊቨርፑል አርሰናል፣ ማንችስተር ሲቲ፣ ቼልሲና ኒውካስትል ዩናይትድ እስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ውድድራቸውን በማጠናቀቃቸው፤ በቀጣዩ ዓመት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋሉ፡፡ የዩሮፓ ሊግ አሸናፊው ስፐርስም የመድረኩ ተሳታፊ ነው፡፡ ሳውዛምፕተን፣ ኢፕስዊች ታወን እና ሌስተር ሲቲ ደግሞ ከፕሪምየር ሊጉ ወደ ሻምፒዮንፕ የወረዱ ክለቦች ናቸው፡፡

ሊጉ ዓመቱን ያጠናቀቀው ለኮከቦች እውቅና በመስጠት ነው፡፡ ሊቨርፑል የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ የሞ ሳላህ የግብ ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ ግብጻዊ አጥቂ በውድድር ዓመቱ 29 ግቦችን አስቆጥሮ የወርቅ ጫማውን ለአራተኛ ጊዜ ወስዷል፡፡ ሳላህ ግብ ከማስቆጠር ባሻገር 18 ለግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ሰጥቶ በአጠቃላይ በ47 ግቦች ላይ ተሳትፎ የዓመቱ ኮከብ ተጨዋች ሽልማትንም አሸንፏል፡፡ የክለብ አጋሩ ሪያን ግራቨንበርች በበኩሉ የዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጨዋች ሽልማትን አሸንፏል፡፡

የአርሰናሉ ዴቪድ ራያና የኖቲግሃም ፎረስቱ ማትስ ሴልስ በ13 ጨዋታዎች ላይ ግብ ሳይቆጠርባቸው በመውጣታቸው የወርቅ ጓንት ሽልማቱን በጋራ ወስደዋል፡፡ ፕሪምየር ሊጉ ሪከርዶች ተመዝግበውበት ነው የተጠናቀቀው፡፡

ሶስት ተጨዋቾች በድምሩ 36 ቢጫ ካርዶችን የተመለከቱበት ዓመት ነው፡፡ የኢፕስዊች ታወኑ ሊያም ዴላፕ፣ የሳውዛምፕተኑ ፍላይን ዶውንስና የፉልሃሙ ሳሳ ሉኪች እያንዳንዳቸው 12 12 ጊዜ በቢጫ ካርድ ተገስጸዋል፡፡ የአርሰናሉ ሊዊስ ስኬሊ፣ የማንችስተር ዩናይትዱ ብሩኖ ፈርናንዴዝና የሳውዛምፕተኑ ጃክ ስቴፈንስ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ቀይ ካርዶችን የተመለከቱ ተጨዋቾች ሆነው ዓመቱ በሪከርድ መዝግቧቸዋል፡፡

በውድድር ዓመቱ 99 ቢጫ ካርዶች የተመዘዙበት ቼልሲ ከፍተኛውን ሲይዝ 57 ጊዜ ብቻ በቢጫ ካርድ የተገሰጸው ማንችስተር ሲቲ ዝቅተኛውን ደረጃ ይዟል፡፡ ስድስት ተጨዋቾችን በቀይ ካርድ ያጣው አርሰናል ዓመቱን በመጥፎ ሪከርድ ሲያሳልፍ ወደ ሻምፒዮንሺፕ የወረደው ሌስተር ሲቲ ብቸኛው አንድም ቀይ ካርድ ያልተመዘዘበት ክለብ ሆኖ ነው ዓመቱ የተጠናቀቀው፡፡

በታምራት አበራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review