የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሁለት ቀናት በኋላ ሊጥሉ ያቀዱት ታሪፍ የንግድ ጦርነትን ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ስጋት አጭሯል፡፡
ቻይና በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ፍላጎት ቢኖራትም የሚመጣውን ፈተና ለመጋፈጥ ዝግጁ መሆኗን ገልፃለች።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሁለቱ ግዙፍ የዓለም ምጣኔ ሀብት ባለቤት ሀገሮች መካከል የሚታየውን የንግድ ጉድለት ለመሙላት ከቻይና ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚያደርጉት የቀረጥ ጭማሪ እስከ 60 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡
ረቡዕ ዕለት ይወሰዳል ተብሎ የሚጠበቀው እርምጃም ቤጂንግን ብቸኛ ተሰላፊ እንደሚያደርጋት ነው የተገለጸው፡፡
ይሁንና ትራምፕ ቻይና ቲክ ቶክ የተሰኘውን ማህበራዊ ሚዲያ ለአሜሪካ ለመሸጥ ከተስማማች ቀረጥ ይቀነስላታል በሚል ሰፊ መደራደሪያ አድርገው አቅርበውታል፡፡
ቲክ ቶክን ለመግዛት የሚደረገው ድርድርም እስከ ቅዳሜ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ይጠናቀቃል ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ አያይዘውም ምንም እንኳን ቻይና ለአሜሪካ የቴክኖሎጂ እና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ጥብቅ ቁጥጥር ብታበጅም፣ ከፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ጠንካራ ግንኙነት አለን ማለታቸውን የሲኤንኤን ዘገባ አመላክቷል፡፡
በወርቅነህ አቢዮ