ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ከተመለሱ አንድ ወር አልፏቸዋል፡፡ በተለይም በአምስተኛው ሳምንት ቆይታቸው አስገራሚ ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡
የመጀመርያው የዩክሬኑን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪን “አምባገነን ” ሲሉ መጥራታቸው ነው፡-
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ አሜሪካ እና ሩሲያ ያደረጉት ውይይት ዩክሬንን በማግለሉ ምክንያት ተገቢ አለመሆኑን መግለፃቸውን ተከትሎ ነው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‘አምባገነን’ መሪ ሲሉ ዘለንስኪን የተቿቸው፡፡
ዘለንስኪ በዩክሬናዊያን ዘንድ ያላቸው ቅቡልነት እጅግ መውረዱን ትራምፕ ተናግረዋል፡፡
የፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የሥልጣን ዘመን ያበቃው በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2024 ግንቦት ወር ላይ ቢሆንም ሀገሪቱ ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ከሩሲያ ጋር የገባችበትን ጦርነት ተከትሎ የምትተዳደረው በወታደራዊ ህግ ነው፡፡
ይህ የዩክሬን አካሄድ ጀርመንን ጨምሮ ከበርካታ ሀገራት ትችት እየቀረበበት ይገኛል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ኪዬቭን ያገለለ ውይይት ከሞስኮ ባለሥልጣናት ጋር ማድረጋቸው ሌላኛው መነጋጋሪያ ነበር፡፡
ባሳለፍነው ማክሰኞ እለት የአሜሪካና ሩሲያ ባለሥልጣናት ከጦርነቱ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ዩክሬን ባልተጋበዘችበት ለብቻቸው መክረዋል፡፡
በሳዑዲ ዓረቢያ በተካሄደው የሠላም ውይይት ላይ የዘለንስኪ መገኘት አስፈላጊ እንዳልነበር ትራምፕ መናገራቸውም ይታወሳል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ ውይይቱ ሠላም ለማምጣት አንድ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡
ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ እስራኞችን ከሩሲያ ጋር መለዋወጣቸው ነው፡፡ በሞስኮ አየር ማረፍያ ካናቢስ ይዘው በመገኘታቸው ታስረው የነበሩ የአሜሪካ ዜግነት ያለውን የ28 ዓመት ወጣት ከሳዑዲ ዓረቢያው ውይይት ቀደም ብሎ ሩሲያ መልቀቅ ችላለች፡፡
አሜሪካ በበኩሏ ከቢትኮይን ግብይት ጋር ተያይዞ በፈረንጆቹ 2017 ያሰረችውን ሩሲያዊ ዜግነት ያለው አሌክሳንደር ቪኒክ የተባለ ሰው እንደምትፈታ ቃል ገብታለች፡፡
ሌላኛው የፕሬዝደንቱ ውሳኔ የኒውዮርክን በተወሰኑ አካባቢዎች የተሽከርካሪ መጨናነቅ ላይ የወጣውን መመሪያ መሻራቸው ነው፡፡
በኒውዮርክ በተወሰኑ የከተማዋ አካባቢዎች የተሽከርካሪ ፍሰት የሚገድብ እና ቅጣት የሚጥለውን መርህ መሻራቸው በዚሁ ሳምንት የተሰማ ዜና ነው፡፡
ትራምፕ” ከእንግዲህ የኒውዮርክ የተሽከርካሪ ቅጣት መርህ አብቅቷል፤ ኒውዮርክ ነጻ ናት፤ ረጅም እድሜ ለንጉሱ ” ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
የትራምፕን ንግግር ተከትሎ የኒውዮርክ አስተዳዳሪ ኬቲ ኦቹል “እኛ ህግ የምናውቅ ህዝብ ነን፣ በንጉስ አንመራም፣ ፍርድ ቤት እናገኝሃለን” ብለዋል፡፡
የድንበር ተሻጋሪ እስረኞች ቁጥር መቀነስ የዚሁ ሳምንት ዐበይት ጉዳይ ነበር፡፡ በአሜሪካ – ሜክሲኮ ድንበር ላይ የሚተላለፉ ፍልሰተኞች ቁጥር ለመጀመሪያ ጊዜ በጥር ወር ላይ ቀንሶ ታይቷል፡፡
በድንበር አካባቢ ታህሳስ ወር ላይ 47ሺ የነበረው የስደተኞች ቁጥር በጥር ወር ወደ 29 ሺ ሊቀንስ ችሏል፡፡ ይህም ከፈረንጆቹ 2020 ወዲህ ትንሹ ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ትራምፕ ጥር 20 ነው ባይደንን ተክተው ወደ ነጩ ቤተ መግስት ያመሩት ፡፡ ከስደተኞች ጋር ተያይዞ የመጣው ለውጥ የወሰዱት ፈጣን እርምጃ ያመጣው ሳይሆን እንዳልቀረ ይገለጻል፡፡
በሺዎቸ የሚቆጠሩ የፌዴራል ሠራተኞችን ከሥራ ማሰናበታቸውም ሌላኛው መነጋገሪያ ጉዳይ ነው፡፡
የትራምፕ አስተዳደር እና የፌዴራል ተቋማት ወጪ ቁጠባን የሚመሩት ኤለን መስክ ወጪ ሊቀንስ ይችላል ያሉትን እርምጃ መውሰዳቸውን ቀጥለዋል፡፡
5ሺ የሚሆኑ የሀገር ውስጥ ገቢ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ባሳለፍነው ዓርብ ከሥራ እንደሚሰናበቱ ይጠበቅ ነበር፡፡
ፔንታጎን በበኩሉ 4500 በሙከራ ጊዜ ቅጥር ላይ ያሉ ሠራተኞቹን በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ቀናት ላይ አሰናብታለሁ ብሏል፡፡
በአሜሪካ ብሔራዊ ፓርክ አገልግሎት ውስጥ ይሰሩ የነበሩ 1000 ሠራተኞችም ባሳለፍነው ሳምንት ከሥራ ውጭ ተደርገዋል፡፡
በዚህ ያላበቃው የትራምፕ አስተዳደር በሀገሪቱ የአቪየሽን መሥሪያ ቤት ያሉ ሠራተኞችን በማሰናበት ቀጥሏል፡፡ የተቋሙ ሃላፊ ድርጊቱን “አሳፋሪ “ሲሉ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
የፌዴራል መንግስት ወጪ ቅነሳ ሀሳብ በብዙዎች ዘንድ የሚደገፍ ሀሳብ ቢሆንም የኤለን መስክ ተቋም የጀመረው መንገድ ምን ያህል ርቀት ያስኬዳል የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡
በደቡበ አፍሪካ በተካሄደው የቡድን 20 ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ አሜሪካ አለመሳተፏ የተሰማው በዚሁ ሳምንት ነው፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የቡድን 20 ሀገራት የውጭ ጉዳይ ስብሰባን ደቡብ አፍሪካ ማስተናገዷ ይታወሳል፡፡
በስብሰባው ላይ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ተገኝተዋል፡፡
አሜሪካ ግን ተወካይ ሳትልክ ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ኤምባሲ ተወካይ በኩል መታደሟ ተሰምቷል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንተ በዚሁ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ዓለም አቀፍ የትብብር ምላሽ ወጥነት እንደሚጎድለው አንስተዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ቻርተር ለተደነገገው ሁሉንአቀፍ መፍትሔ እና ዓለምዓቀፍ ህግ መከበር ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዝደንቱ ጀነራል ማባረራቸው፤ ጀነራል ብሮውን የተባሉ የፕሬዝዳንት እና የመከላከያ ዋና ፀሀፊ አማካሪ የሆኑትን በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸውን 2ኛውን ጥቁር ሰው ማባረራቸውን በራሳቸው ማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ አስታውቀዋል፡፡
የአሜሪካ እና እንግሊዝ ጥምር ዜግነት ያለው እና በማህበራዊ ሚዲያ ተፅእኖ ፈጣሪ የሆነው አንድሪው ቴት በተባለ ግለሰብ ላይ በቀረበው የክስ ጉዳይ ላይ ጣልቃገብነትን መከልከላቸው፣ የአሜሪካ ግብርና ዲፓርትመንት ሠራተኞችን መልሶ ለመቅጠር መሞከራቸው፣ አይ ቪ ኤፍ የተሰኘ የመካንነት ችግር ላለባቸው ሴቶች ፅንስ በማህፀን ውስጥ ለማሳደግ የሚከፈለውን የገንዝብ መጠን ለመቀነስ መወሰናቸው፣ ዶክመንት ለሌላቸው ስደተኞች የሚደረገውን ድጋፍ ማቋረጣቸው፣ የመከላከያ በጀት 50 ቢሊዮን ዶላር እንደሚቀንሱ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ከውሳኔ በመድረስ መነጋገሪያ ሆነው መሰንበታቸውን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡
በማሬ ቃጦ