የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በበይነ መረብ ለመስጠት በቂ ዝግጅት መደረጉን የአዲሰ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ተማሪዎች የተሻለ የእውቀት ባለቤት ከቴክኖሎጂም ጋር የተግባቡ ይሆኑ ዘንድ በአብርሆት ቤተ መጽሀፍት የሞዴል ፈተና ተሰጥቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ(ዶ/ር)፣ በትምህርት ቤቶች በቂ ኮምፒዩተሮችን ማሰራጨት አስተማማኝ የኔትወርክ ዝርጋታን እውን ማድረግ እና ተማሪዎች ተደጋጋሚ ልምምዶችን እንዲያደርጉ ተሰርቷል ብለዋል፡፡
ከሰሞኑ የበይነ መረብ የሞዴል ፈተና ለተፈታኞች እየተሰጠ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ይህም አንድም ትምህርታቸውን እንዲከልሱ በሌላ መልኩ ከቴክኖሎጂው ጋር በመላመድ ለዋናው ፈተና ዝግጁ እንዲሆኑ እድል የፈጠረ ነዉ ብለዋል፡፡

በቀጣይ ቀሪ ጊዚያትም ተማሪዎችን ለተሻለ ውጤት ዝግጁ የማድረግ ስራ ይሰራል ያሉት ኃላፊው፣ ለተማሪዎች ውጤት የተቃና መሆን ወላጆች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉ ተማሪዎችም የበይነ መረብ ፈተናው ኩረጃን የሚያስቀር እና የጊዜ አጠቃቀምን የሚያሻሽል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለፈተናው በቂ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸዉንም ተናግረዋል፡፡
በተመስገን ይመር