የ2017 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 86 በመቶ ውጤታማ አፈፃጸም የታየበት ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing የ2017 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 86 በመቶ ውጤታማ አፈፃጸም የታየበት ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ህዳር 3/2017 ዓ.ም

የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸማችንን ድክመት እና ጥንካሬዎቻችንን ከነመንስዔዎቻቸው በመለየት ገምግመናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ገልጸዋል፡፡

ከንቲባዋ በመልዕክታቸው የስራ ባህላችን ወጪ ቆጣቢ ፣ጥራትና ባጠረ ጊዜ ውስጥ የሰራናቸው ስራዎች ከተማችንን ለነዋሪው ምቹ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡

አዲስ አበባን የቱሪስት መዳረሻ፣ ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል ለማድረግ እና የሀገራችንን ገፅታ ለመገንባት የሰራናቸው የኮሪደር ልማትና ከተማዋን መልሶ የማደስ ስራዎቻችን ዉጤታማ ሆነዉ ከተማችን በሩብ አመቱ ብቻ 20 የተለያዩ አህጉራዊና አለምአቀፍ ኮንፍረንሶችን በብቃት ማስተናገድ አስችሏታል ብለዋል።

በዚህ ሩብ ዓመት በየተቋማቱ አቅደን ከፈፀምነዉ አንፃር 86 እጅ ዉጤታማ አፈፃፀም የታየበት ሲሆን፤ ከህዝብ ጋር ተቀራርበን የሰራንበት፣ የአመራር ቅንጅት፣ የስራ ባህላችን መለወጥ እና ከተማችንን የሚመጥን የስማርት ከተማ ግንባታ ስራዎቻችን ስኬት ያገኘንባቸው ናቸው ሲሉም ገልፀዋል::

በኮሪደር ልማት ምክንያት ለኑሮ ከማይመች ጎስቋላ አካባቢ ያነሳናቸው ነዋሪዎቻችንን ለኑሮ ምቹ የሆነ ንጹህ የመኖሪያ ቤት እና አካባቢ እንዲያገኙ ማድረግ የቻልን ሲሆን፤ ከተማ ብቻ ሳይሆን የሰው ህይወት አብሮ የታደሰበት አፈፃፀም መሆኑንም ገምግመናል በማለትም አክለዋል::

ፈተናዎችን እየተሻገርን ባሳካናቸው ስኬቶች ሳንረካ የአገልግሎት አሰጣጣችንን ከህዝባችን ፍላጎትና ካስቀምጥነው ስታዳርድ አኳያ፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራር ያልተሻገርናቸው መሆናቸውን አምነን ለመከላከል የዘረጋነዉ አሰራር እንዲሁም ነዋሪው የሰጠንን ጥቆማና አስተያየት መሰረት በማድረግ የሰራናቸው ስራዎች ፍሬ ማፍራት ጀምረዋል ብለዋል፡፡

አሁንም አፅንኦት ሰጥተን ችግሩን በሚመጥን ደረጃ በዘላቂነት ለማረም የሚያስችል የአመራር ቁመና ለመፍጠር፣ ግልፅነትን እየጨመርን እና ነዋሪውን እያሳተፍን መስራት የሚያስችል አቅጣጫም አስቀምጠናል ነው ያሉት ከንቲባዋ::

በተጨማሪም በተቋም ግንባታ፣ የሰው ተኮር ስራዎችን ማጠናከር፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነትን በመቀነስ፣ ገቢ አሰባሰብ ማሻሻል፣ የንግድ ስርአቱን ማጠናከር፣ ለነዋሪዎቿ የተመቸች ከተማ መገንባት እንዲሁም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በመጨረስ ወደ አገልግሎት ማስገባት እና የ2ተኛ ዙር ኮሪደር ስራን በጥራት እና በፍጥነት ማጠናቀቅ በቀጣይ በልዩ በትኩረት የምንሰራቸው ስራዎች ናቸው ሲሉም አብራርተዋል::

አገልግሎት አሰጣጣችንን ይበልጥ ቀልጣፋና ከሌብነትና ብልሹ አሰራር የጸዳ በማድረግ በትጋትና በታማኝነት በማሳተፍ መስራታችንን አሁንም አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም ገልጸዋል::

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review