ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 35ኛ መደበኛ ስብሰባ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ያቀረቡትን የፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ የበጀት መግለጫ አዳምጧል፡፡
የ2018 በጀት ዓመት የፌደራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ተግባራዊ እተደረገ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና የፊዚካል ፖሊሲን ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
ለ2018 በጀት ዓመት የተዘጋጀው ረቂቅ በጀት የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አካል የሆነውን የ2016-2018 የልማትና ኢንቨስትመንት እቅድ እና የፕሮግራም በጀት በማጣጣም የተቀመጡ ግቦችና አቅጣጫዎችን ከማስፈጸም አኳያ እና ሊኖር የሚችለውን የሀብት መጠን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠል፣ የመንግስት ብድር ጤናማ እንዲሆን ከአበዳሪዎች ጋር የዕዳ ሽግሽግ ድርድር ማድረግ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሚያስከትለውን ጫና ለመቀነስ የማህበራዊ ወጪ ድጎማን ማስቀጠል በትኩረት ከሚሰሩት ውስጥ ጠቅሰዋል።
ከ2017 በጀት አንጻር የ34 ነጥብ 4 በመቶ እድገት እንዳለው አስታውሰዋል፡፡
ወጪው የሚሸፈነው ከ80 በመቶ በላይ ከአገር ውስጥ ገቢ ሲሆን አዳዲስ የታክስ ምንጮችን ወደ ገቢ ስርዓቱ በማስገባትና የነበሩትን በማጠናከር ገቢን ለመጨመር እንደሚሰራ አብራርተዋል።
በዚህም በ2018 በጀት አመት አጠቃላይ 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።
ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የተመደበላቸውን በጀት ለታለመለት አላማ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
በመሆኑም የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 1 ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።
ረቂቅ በጀቱ ለዝርዝር እይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።