የ3ተኛ ዙር የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ሰልጣኞች ተመረቁ

AMN – ጥር 3/2017 ዓ.ም

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በ2016 የክረምት መርሃ ግብር ባካሄደው ስስተኛው ዙር የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ፕሮግራም ሲሰለጥኑ የቆዩ 237 የሚሆኑ የሳይበር ደህንነት ባለልዩ ተሰጥኦ ታዳጊ ወጣቶችን አስመርቋል፡፡

በተጨማሪም ከ40 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በዛሬው ዕለት ስልጠናውን መወሰድ ጀምረዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጉታ ፣ በክረምት መርሃ ግብር በሳይበር ታለንት ሰልጥነው የተመረቁ ባለተሰጥኦ ታዳጊዎች ወደ አዲስ ምዕራፍ በመሸጋገራችሁ የእንኳን ደስ አላቹህ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሀገር ከሳይበር ታለንት ተመራቂዎች ብዙ ትጠብቃለች በማለት ለዚህ ስኬትም የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ተመራቂዎች በሰመር ካምፕ መርሃ ግብር በተናጠል በተለያዩ ዘርፎች ፈጠራዎች በመስራት አበረታች ውጤት ማስመዝገባቸውን ያስታወሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ በዚህ አዲስ ምዕራፍ በየዘርፉና በዝንባሌያቸው መሰረት በቡድን ትልቅ ሀገር በቀል ፕሮጀክት ተሰጥቷቸው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

አያይዘውም፣ በዚህ አዲስ ምዕራፍ አስተዳደሩ በግንባር ቀደምትነት የታዳጊዎችን የፈጠራ ችሎታና አቅም ለሀገር ጥቅም እንዲውል ተቋማት እና የግል ባለሃብቶች ባለልዩ ተሰጥኦ ታዳጊዎችን በማገዝ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል ።

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደረጄ እንግዳ በበኩላቸው፣ ፈተናዎች ቢኖሩም ፈተናዎችን ተቋቁማቹሁ እና ለችግሮቹ የመፍትሄ አካል የሆናቹሁ የነገ ሃገር ተረካቢ በመሆናቹሁ ልትኮሩ ይገባል ብለዋል።

ባለልዩ ተሰጥኦ ታዳጊዎችም የተጣለባቸውን ሀገራዊ አደራና ኃላፊነት በቁርጠኝነት ለመወጣት ቃል ገብተው አስተዳደሩ ለሰጣቸው እድል እና ላደረገላቸው እገዛ ምስጋና አቅርበዋል።

የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ስልጠና ለመውሰድ ከ8ሺ በላይ ሰልጣኞች ተመዝግበዋል።

በመሃመድኑር ዓሊ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review