ለበዓል ወንድሟን ለመጠየቅ በመጣችበት አጋጣሚ ከጎረቤት የ4 ዓመት ህፃን ልጅ በከረሜላ አታላ የሠረቀችውን ተጠርጣሪ ከነተባባሪዋ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።
ሕፃን ኢዮሃ አቡሽ ሚያዚያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት አካባቢ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተለምዶ መሳለሚያ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ካለው የወላጆቹ መኖሪያ ግቢ እየተጫወተ በደንገት እንደጠፋ ነው የተገለፀው፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሚዲያ እንደተናገሩት፣ በዕለቱ ለዳግም ትንሣኤ ወንድሟን ለመጠየቅ የመጣች አንዲት ግለሰብ፣ ልጁን ሰርቃ ወደ አዳማ እንዲወሰድ ማድረጓን ገልጸዋል፡፡
ይሁንና ግለሰቧ ድርጊቷን ለመሸፈን ወደ አካባቢው በመመለስ የጠፋውን ህፃን አብራ መፈለግ እንደጀመረችም ነው የተናገሩት፡፡
ግለሰቧ፣ የጎረቤት ልጆችን በሙሉ ወደ ሱቅ በመውሰድ ከረሜላ፣ ፊኛና የተለያዩ ጣፋጭ ነገሮችን በመግዛት ወደ ግቢው ስትመልሳቸው ማየታቸውን እና ልጃቸውን ግን እንዳላዩት የሕፃን ኢዮሃ እናት ወይዘሮ ሰብለ ሰንበቴ ለፖሊስ እንደተናገሩ ገልጸዋል፡፡
ፖሊስ በደረሰው መረጃም አስፈላጊውን ማጣራት ካደረገ በኋላ፣ ግለሰቧ እንዳትሰወር በጥንቃቄ በመከታተል ፖሊሳዊ ጥበብ በመጠቀም ህፃኑ የሚገኝበትን ቦታ በማረጋገጥ በ48 ሰዓታት ውስጥ የጠፋውን ልጅ ጨምሮ ተጠራጣሪዋን ገንዘብ ክፈሉ እያለች በስልክ ከምትደራደረው ግብረ አበሯ ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉን ኮማንደር ማርቆስ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን በቀጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ልጆች የወላጆች ወይም የአሳዳጊዎች ብቻ ሳይሆኑ የማህበረሰቡም ጭምር ሀብት በመሆናቸው፣ የልጆች አሳቢና ተንከባካቢ መስለው ድብቅ የሆነ እኩይ ተግባር የሚፈፅሙ አንዳንድ ግለሰቦች ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ ወላጆችም ሆኑ መላው ሕብረተሰብ ለሕፃናት ልዩ ክትትልና ጥበቃ በማድረግ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በታምራት ቢሻው