በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላለፉት ሶስት ቀናት ሲሰጥ የቆየው የ2017 የትምህርት ዘመን የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተጠናቋል፡፡
ፈተናው በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ 192 የመፈተኛ ጣቢያዎች ለተከታታይ ሶስት ቀናት ሲሰጥ ቆይቶ በሰላም መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዘላለሞ ሙላቱ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች የተመደቡ የጸጥታ አካላት ፣ ፈታኞች ፣ የጣቢያ ኃላፊዎች ፣ ሱፐርቫይዘሮችና የፈተና አስፈጻሚዎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በትጋት በመወጣታቸው ምስጋና ያቀረቡት ሃላፊዉ ፈተናው በጭር ጊዜ ውስጥ ታርሞ ይፋ እንደሚደረግም አስታዉቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ አበበ ቸርነት በበኩላቸዉ የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተናን የወሰዱ ተማሪዎች ፈተናዉን ካጠናቀቁ በኋላ የተለያዩ ችግኞችን በመትከል አረንጓዴ አሻራቸዉን ማኖራቸዉን ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ እንዳስታወቁት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የ2017 የትምህርት ዘመን የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተናን የወሰዱ ተማሪዎች ፈተናዉን ካጠናቀቁ በኋላ አሻራቸዉን ማኖራቸዉን ጠቁመዉ ተመሳሳይ መርሃ ግብር በሌሎች ክፍለ ከተሞችም የሚካሄድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ