የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እሁድ እለት እንዳስታወቀዉ ዋሽንግተን በቅርቡ በካሽሚር ጥቃት መሰንዘርን ተከትሎ በህንድና ፖኪስታን መካከል አለመግባባት እየተፈጠረ ባለበት ወቅት ከሁለቱ ሃገራት ጋር በመገናኘት “ተጠያቂነት ያለው መፍትሄ” ወደተባለው ሃሳብ እንዲመጡ አሳስቧል ።
የዩኤስ መንግስት ከጥቃቱ በኋላ በግልጽ ለህንድ ድጋፉን ቢገልጽም ፓኪስታንን ግን አልነቀፈም። ህንድ ሚያዝያ 22 በህንድ በሚተዳደረው ካሽሚር ከሁለት ደርዘን በላይ ሰዎችን ለገደለዉ ጥቃት ፓኪስታንን ተጠያቂ ብታደርግም ፓኪስታን ግን ኃላፊነቱን በመካድ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቃለች።
ተንታኞች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ዋሽንግተን እንደ ዩክሬን እና ጋዛ ባሉ አለምአቀፍ ቀውሶች ላይ ባተኮረችበት ወቅት በዚህ ግጭት ጠንከር ያለ ጣልቃ ገብነት ላታደርግ ትችላለች ተብሎ እየተነገረ ነዉ፡፡
ፓኪስታን የአየር ክልሏን ለህንድ በረራዎች መዝጋቷን እና ህንድ የኢንዱስ ውሃ ስምምነትን ማገድን ጨምሮ ሁለቱም ሀገራት የአጸፋ እርምጃ ወስደዋል። አሜሪካ ለህንድ የምትሰጠው ያልተቋረጠ ድጋፍ በሁለቱ ጎረቤት ሃገራት መካከል ወታደራዊ መስፋፋትን ሊያበረታታ ይችላል የሚል ስጋት እየጨመረ ነው ሲል ዘ ጃፓን ታይምስ ዘግቧል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በሃገራቱ ምካከል ያለውን ጉዳይ እየተከታተልን ነው ያሉ ሲሆን ዋሽንግተን ከህንድ ጎን እንደምትቆም እና በፓሃልጋም የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት አጥብቃ ታወግዛለች ሲሉም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ከሰጡት አስተያየት ጋር ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።
በሊያት ካሳሁን