ዩክሬን ለሠላም ንግግር ዝግጁ መሆኗን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናገሩ

You are currently viewing ዩክሬን ለሠላም ንግግር ዝግጁ መሆኗን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናገሩ

AMN – የካቲት 26/2017 ዓ.ም

የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ለሠላም ንግግር ዝግጁ መሆናቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ገልጸዋል፡፡

ትራምፕ በትናንትናው እለት በኮንግረሱ ፊት ቀርበው ባደረጉት ንግግር ሠላምን ከዩክሬናዊያን በላይ የሚሻ አለመኖሩን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ከላኩላቸው ደብዳቤ ላይ ጠቅሰው ተናግረዋል፡፡

የሠላም ንግግሩ የመጨረሻ ግብ ሠላምን ለማምጣት እስከሆነ ድረስ ዘለንስኪ ከሩሲያ ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ለመወያየት ዝግጁ ነኝ ማለታቸውንም አንስተዋል፡፡

በተመሳሳይ ከሩሲያ ጋር ጠንከር ያለ ውይይት አድርገው አዎንታዊ ምላሽ ማግኘታቸውን የተናገሩት ትራምፕ ይህን ትርጉም የሌለውን ጦርነት እና ሞት ማስቆም ይገባናል ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኮንግረሱ ባደረጉት ንግግር ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ ምድር የተካሄደውን ከባዱን ጦርነት እንዴት ያስቆሙታል ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ሊሰጥ የሚችል ዕቅድ ያቀርባሉ ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ይህ ሳይሆን ቀርቷል፡፡

ዩክሬን ከአሜሪካ ጋር የማዕድን ስምምነት ላይ ለመፈረም ዝግጁ መሆኗን አንስተው በአንጻሩ አሜሪካ ለዩክሬን መከላከያ ድጋፍ እንድታደርግ ያስችላል ብለዋል፡፡

በመሪዎቹ መካከል በተካረረው አለመግባባት ምክንያት አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ ማቋረጧን ትላንት መግለጿ ይታወቃል፡፡

የአሜሪካንን ውሳኔ ተከትሎ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ጋር ሠላምን ለማምጣት እንሰራለን ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

ዘለንስኪ ለትራምፕ በጻፉት ደብዳቤ አሜሪካ የዩክሬንን ሉዓላዊነት እና ነጻነት ለማስጠበቅ የዋለችውን ውለታ እንደሚያከብሩ ገልጸዋል፡፡

በኋይት ሀውስ ሁለቱ መሪዎች ያደረጉት ግራ አጋቢውን ውይይት አስመልክተውም የሚፀፅት እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ይሁንና ብዙዎች እንደሚገምቱት መጥፎ እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡

አሁን በፍጥነት ችግሮችን አርመን ከአሜሪካ ጋር የምንሠራበት ወቅት ነው ማለታቸውን ሮይተርስ አስነብቧል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review