AMN – የካቲት 28/2017 ዓ.ም
ዩክሬን እና አሜሪካ በቀጣዩ ሳምንት በሳዑዲ ዓረቢያ ተገናኝተው ይወያያሉ፡፡
ዩክሬን እና ሩሲያ ከሠላም ንግግር ውጭ ሌላ ምርጫ እንደሌላቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናግረዋል፡፡
በቀጣዩ ሳምንትም የአሜሪካ እና ዩክሬን ባለሥልጣናት በሳዑዲ ዓረቢያ ተገናኝተው የሩሲያ-ዩክሬን ግጭት ዙሪያ የሠላም ንግግር ለማስጀመር መሠረት የሚጥል ምክክር እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
ትራምፕ እና ዘለንስኪ በነጩ ቤተ መንግስት በመሪዎች መካከል ያልተለመደ እና ዱላ ቀረሽ የሚመስል ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ ባሳለፍነው ሳምንት በመሪዎቹ መካከል ሰፊ ልዩነት ተፈጥሮ ቆይቷል፡፡
በመሪዎቹ መካከል በተፈጠረው ልዩነት ምክንያት አሜሪካ ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ ላለማድረግ ከውሳኔ መድረሷም ይታወቃል፡፡
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ እለት ለኮንግረስ ባደረጉት ንግግር ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በድርጊታቸው ተፀፀተው ለሠላም ንግግር ዝግጁ መሆናቸው የሚገልፅ ደብዳቤ ልከውልኛል ብለው ነበር፡፡
በቀጣዩ ሳምንት በሳዑዲ ዓረቢያ እንደሚገኙ የገለፁት የፕሬዝዳንት ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ስቲቭ ዊትኮፍ በውይይቱ ለሠላም ንግግሩ አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በበኩላቸው በቀጣዩ ሰኞ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ እንደሚያቀኑ እና ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ ተናግረዋል፡፡ ዩክሬናዊያን ሠላምን አጥብቀው እንደሚሹም አክለዋል፡፡
ከሳምንት በፊት ዘለንስኪ ነጩን ቤተ መንግስት ለቀው እንዲወጡ ከተደረገበት አነጋጋሪው መድረክ ወዲህ የአሜሪካ እና ዩክሬን መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በሳዑዲ ዓረቢያ ፊት ለፊት ተገናኝተው እንደሚነጋገሩ አልጀዚራ ነው የዘገበው፡፡