የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት በተለምዶ ጉራራ ኪዳነ ምህረት በሚባለው አካባቢ ያለው አደባባይ ዙሪያው ሁሌም ደማቅ ነው፡፡ የእግረኛ መንገዶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ለንግድ ሥራ በወጡ እናቶች፣ ወጣት ሴትና ወንዶች ይያዛል። የታክሲ እና የከተማ አውቶብሶች መጫኛ እና ማውረጃ ስፍራም ነው፡፡ ቀን ላይ በአብዛኛው ድንች፣ ሽንኩርት፣ ቅመማ ቅመም፣ የባልትና ውጤቶች፣ እርጥብ ሣር፣ አልባሳት የመሳሰሉ የምርት ዓይነቶችን የያዙ ነጋዴዎች በአነስተኛ ምንጣፍ ላይ በመዘርጋት ገዢን ይጠባበቃሉ፡፡ ሰዓቱ እየገፋ ሲሄድ ደግሞ በእጅ የሚገፋ ባለ አንድ ጎማ ጋሪ ላይ የተጫኑ ፍራፍሬዎች ሙዝ፣ ሃባብ፣ ብርቱኳን፣ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ የተቆራረጠ ሸንኮራ እና መሰል የምርት ዓይነቶችን የያዙ ነጋዴዎች አካባቢውን ይቀላቀሉታል፡፡ የግብይት ሁኔታውም እየደመቀ እና እየደራ ይሄዳል፡፡ ለእንቅስቃሴ አዳጋች የሆነ ሁኔታም ይፈጠራል፡፡
ዘወትራዊ የሚመስለው የጉራራ ኪዳነ ምህረት አካባቢ ድባብ፤ ቅዳሜ እና እሁድ የገበያ ማዕከልነት ድምቀቱ ይጎላል። በእነዚህ ሁለት ቀናት ምርታቸውን እንዲሸጡ የተፈቀደላቸው የግብርና ምርት አቅራቢዎች፣ የመሰረታዊ ሸማች ሕብረት ሥራ ማህበራት፣ በአነስተኛ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች በዋናው አስፋልት ላይ ድንኳኖችን በመጣል እና ሸራዎችን በመወጠር የተለመደውን የግብይት ሥራ ይከውናሉ። ቁጥሩ ቀላል የማይባል ሸማች በግብይቱ ይሳተፋል። የሚፈልገውን ሸምቶ ይሄዳል። ነጋዴዎቹም ብዛት ካለው አቅራቢ ጋር በመወዳደር ሽያጭ ይፈፅማሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በጉራራ ኪዳነ ምህረት አካባቢ ያለውን አይነት የየዕለት የገበያ እንቅስቃሴ የሚመስል ሁነት በሌሎችም የከተማዋ አካባቢዎች ማየት የተለመደ ነው፡፡ ከዚህ አለፍ ሲልም፤ ከደንብ አስከባሪዎች እና ከፀጥታ አካላት ጋር “የሌባና ፖሊስ” ዓይነት ትዕይንት የታጀቡ የንግድ እንቅስቃሴዎችን መመልከትም እንዲሁ፡፡ በእርግጥ ይህን የመሰለው የንግድ እንቅስቃሴ፤ መደበኛ ያልሆነ (ኢ-መደበኛ) ንግድ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ብቻ የሆነና የሚሆን አይደለም፡፡ በሌሎች የዓለም ሀገራት ከተሞችም ይኸው ተግባር የነበረ፣ ያለና የሚኖር ነው፡፡
መደበኛ ስላልሆኑ (ኢ-መደበኛ) ንግዶች እንድናነሳ ምክንያት የሆነን፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በቅርቡ ባካሄደው 4ኛ ዓመት 8ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ካሳለፈባቸው አጀንዳዎች እና ካፀደቃቸው ደንቦች መካከል አንዱ ስለሆነው “መደበኛ ያልሆነ ንግድን ስርዓት ለማስያዝ የወጣው ደንብ ቁጥር 184/2017” የተወሰነ መረጃ ነው፡፡
የዚህን ደንብ መጽደቅ መነሻ በማድረግ ስለደንቡ አስፈላጊነት፣ ከደንቡ መጽደቅ በፊት መደበኛ ያልሆኑ የጎዳና ላይ ንግዶች እንዴት ይመሩ እንደነበር፣ ደንቡ ወደ ተግባር ሲገባ የሚጠበቀው ውጤት እና ተያያዥ ጉዳዮችን መሰረት በማድረግ ጥያቄዎችን ያቀረብንላቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍሰሃ ጥበቡ ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡
“አዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባት ማዕከል ነች፡፡ ታላቁን የመርካቶ ገበያ ጨምሮ በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ ይከናወናል፡፡ በመጠንም፣ በተደራሽነትም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የንግድ እንቅስቃሴ ከሕጋዊነቱ አንፃር ከታየ መደበኛ እና መደበኛ ያልሆነ ተብሎ ሊከፈል ይችላል” ያሉት አቶ ፍሰሀ፤ መደበኛ ተብለው የሚጠቀሱት የንግድ እንቅስቃሴዎች የንግድ ፍቃድ አውጥተው፣ ቋሚ የመሥሪያ ቦታ ኖሯቸው፣ ለመንግስት የሚጠበቅባቸውን ግብር ከፍለው የሚነግዱ፤ በአንፃሩ መደበኛ ያልሆኑ ወይም ኢ-መደበኛ የሚባለው የንግድ ሥራ ከመደበኛ ንግድ ውጪ በጎዳናዎች፣ በአደባባዮች፣ በጥናት ላይ ተመስርቶ ለተወሰነ ጊዜ የንግድ ሥራ እንዲከናወንባቸው በመንግስት በተፈቀዱ ቦታዎች… ላይ የሚከናወን የግብይት ዓይነት መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የኢ-መደበኛ ንግድ ሥራ በቀን ወይም በማታ፣ ቅዳሜ እና እሁድ ወይም በተመረጡ ቀናት የሚከናወን ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ፍሰሃ ማብራሪያ ከሆነ፤ መደበኛ ያልሆኑ ወይም ኢ-መደበኛ በሚባለው የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉትን ነጋዴዎች ወደ ትክክለኛው ሥርዓት ለማስገባት እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀደም ሲል ጀምሮ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል፡፡ ሥራውንም ሕግና ሥርዓት ባለው አግባብ ለማከናወን የሚያስችሉ ደንብ እና መመሪያዎች በሚመለከተው አካል ፀድቀው ተፈፃሚ ሲሆኑ ቆይተዋል፡፡
አሁን ላይ በከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ የፀደቀው መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድን ሥርዓት ለማስያዝ ይረዳ ዘንድ የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ (መደበኛ ያልሆነ ንግድን ስርዓት ለማስያዝ የወጣው ደንብ ቁጥር 184/2017) አዲስ የወጣ ሳይሆን፤ በነባሩ ደንብ ላይ የተደረገ ማሻሻያ ስለመሆኑ ያስታወሱት በንግድ ቢሮ የግብይት ዘርፍ ኃላፊው፤ በነባሩ ደንብ አማካኝነት የሚሠራው የኢ-መደበኛ ንግዶችን ሥርዓት የማስያዝ እንቅስቃሴ የሚጠበቀውን ያክል ውጤት ሊያመጣ ባለመቻሉ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ የኢ-መደበኛ የንግድ እንቅስቃሴ እየተስፋፋ እና እየተበራከተ መምጣቱን አንስተዋል፡፡ ይህንን የኢ-መደበኛ የንግድ እንቅስቃሴ መስፋፋት እና መበራከት ሕጋዊ አሠራርን በተከተለ አግባብ ሥርዓት ለማስያዝ አንዲያግዝ የደንብ ማሻሻያ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ቀድሞ ሲሠራበት የቆየው ደንብ የነበሩበትን ክፍተት እና በማሻሻያው ስለተካተቱት ጉዳዮች በተመለከተ በንግድ ቢሮ የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍሰሃ ጥበቡ እንደገለፁት፤ በሥራ ላይ የነበረው ደንብ ብዙ ክፍተቶች ነበሩበት፡፡ ከክፍተቶቹ መካከል፡- ፈጣን የሆነውን የከተማዋን ዕድገትና ለውጥ የሚያስተናግድ አለመሆኑ፣ የኢ-መደበኛ ንግድ ሥራ ሽግግርን በግልፅ አለማስቀመጡ ወይም በኢ-መደበኛ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት መቼ፣ እንዴት፣ በምን አግባብ ወደ መደበኛ የንግድ ሥርዓት ይሸጋገራሉ?’ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ አለመስጠቱ፣ የኢ-መደበኛ የንግድ ሥራዎችን የመሥሪያ ዘርፎች በግልፅ ተንትኖ አለማካተቱ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
የተሻሻለው ደንብ በሥራ ላይ የነበረውን ጉድለት የሚቀርፍ ነው፡፡ በኢ-መደበኛ ንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሸጋገሩበትን የአሠራር ሥርዓት በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ሽግግሩ በማን እና እንዴት እንደሚከናወንም በግልፅ ተካትቷል፡፡ የሥራው ባለቤትም ተለይቶ ተጠቅሷል፡፡ በኢ-መደበኛ ንግድ ሥራ ውስጥ የሚካተቱ የሥራ ዘርፎች፣ ሥራው የሚከናወንባቸው ቀንና ሰዓት፣ የሥራ ቦታዎች እና መሰል ጉዳዮች በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ የኢ-መደበኛ ንግድ ሥራ እንቅስቃሴዎች በመደበኛው ንግድ ሥራ ላይ ተፅዕኖ በማያሳድር ሁኔታ የሚከናወኑበትን ሥርዓት ለመፍጠር እንዲቻል በተሻሻለው ደንብ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
“ኢ-መደበኛ ንግዶች የራሳቸው የሆነ በጎ ጎን አላቸው፡፡ የንግዱ ማህበረሰብ ራሱንና ቤተሰቡን ለማስተዳደር የሚያስችለውን ገቢ ያስገኙለታል። የንግድ ሥራ የሚለማመድባቸው፣ በኢኮኖሚው አቅሙን የሚያደራጅባቸው እና ወደ ቀጣዩ ደረጃ ለመሸጋገር እንደመስፈንጠሪያ የሚጠቀምባቸው ናቸው፡፡ ከንግድ አሠራሩ እና ሥርዓቱ ጋርም የሚለማመዱበት ሁነኛ መስክ ነው” ያሉት አቶ ፍሰሃ፤ በኢ-መደበኛ ንግድ ሥራ ላይ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ የተሻሻለው ደንብ የሚያስገኛቸውን ተጠባቂ ፋይዳዎችንም ዘርዝረዋል። እንደሳቸው ገለፃ፤ የተሻሻለው ደንብ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን የኢ-መደበኛ ነጋዴዎች እና የፀጥታ ወይም የደንብ አስከባሪዎች ለአደጋ አጋላጭ የሆነ መስተጋብርን ለመቀነስ እና መፍትሄ ለመስጠት ያግዛል። የትራፊክ እንቅስቃሴን መታወክ፣ መጨናነቅ እና የአደጋ ተጋላጭነትን ይቀንሳል፡፡ በኢ-መደበኛ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች በተሰጣቸው ቦታ፣ በተወሰነላቸው ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ሥራቸውን የሚሠሩበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡
የኢ-መደበኛ የንግድ ሥራዎች እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስፋት ከሚተገበርባቸው ቦታዎች መካከል በኮልፌ አካባቢ፣ በቂርቆስ (ለገሀር)፣ ንፋስ ስልክ፣ አቃቂ፣ ለሚ ኩራ እና መሰል አካባቢዎች ያሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ በኢ-መደበኛ ንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ነጋዴዎች ቁጥር 4 ሺህ 831 ይጠጋል፡፡ በአንፃሩ፤ ንግድ ፍቃድ አውጥቶ በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ነጋዴዎች ቁጥር 411 ሺህ አካባቢ ይደርሳል፡፡ የተሻሻለው ደንብ በኢ-መደበኛ የንግድ ሥራ ውስጥ ያሉትን የንግድ ማህበረሰብ በዘርፉ ውስጥ ወቅቱን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዴት እንደሚስተናገዱ ምላሽ የሚሰጥ አሠራርን የማስፈኑን ተግባር እንደሚያቀላጥፍ ይጠበቃል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፤ ከተማ አስተዳደሩ በዘርፉ የሚታዩ ሕገ-ወጥነቶችን ለመከላከል እና ሕጋዊ ስርዓት ለማስያዝ ያግዘዋል፡፡ ለህብረተሰቡ አማራጭ የግብይት ሥፍራዎች እንዲበራከቱ ያደርጋል፡፡ ኢትዮጵያ ታምርት በሚለው ንቅናቄ እያደገ ለመጣው የአገር ምርት ሁነኛ የገበያ ትስስር መፍጠሪያ ይሆናሉ። ለምሳሌ ከውጪ አገራት የሚገቡ ልባሽ አልባሳት እና ጫማዎች በአገር ውስጥ ምርት እንዲተኩ የሚደረግበትን አሠራር መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድን ሥርዓት ለማስያዝ ይረዳ ዘንድ የተዘጋጀው ደንብ ምላሽ ይሰጣል፡፡
በደረጀ ታደሰ