ዶናልድ ትራምፕ በመካከለኛው ምስራቅ ግጭት የሁለት ሳምንታት የጊዜ ሰሌዳ ማስቀመጣቸውን ተከትሎ ዩኬ እና የአውሮፓ ህብረት ከኢራን ጋር ሊነጋገሩ ነው

You are currently viewing ዶናልድ ትራምፕ በመካከለኛው ምስራቅ ግጭት የሁለት ሳምንታት የጊዜ ሰሌዳ ማስቀመጣቸውን ተከትሎ ዩኬ እና የአውሮፓ ህብረት ከኢራን ጋር ሊነጋገሩ ነው

AMN – ሰኔ 13/2017 ዓ.ም

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራን-እስራኤል ግጭትን በተመለከተ ስለሚኖራቸው ሚና ለማሳወቅ የሁለት ሳምንታት የጊዜ ሰሌዳ ማስቀመጣቸውን ተከትሎ ዩኬ እና የአውሮፓ ህብረት ከኢራን ጋር ሊነጋገሩ ቀጠሮ መያዛቸው ተገለጸ።

የዩኬ፣ የፈረንሳይ እና የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከኢራን አቻዎቻቸው ጋር በመገናኘት የኢራን-እስራኤል ግጭትን ማስቀረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሊመክሩ በጄነቫ መቀጣጠራቸው ተነግሯል።

ዛሬ በጄኔቫ በሚደረገው ውይይት፣ የአውሮፓ ሚኒስትሮች የኢራን አቻቸው አባስ አራግቺ ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ውጥረት በሚረግብበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ተሰናድተዋል፡፡

ስብሰባው በታቀደው መሰረት የሚሄድ ከሆነ፣ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በቴህራን እና በምዕራባውያን መንግስታት መካከል የገፅ ለገፅ ንግግር ይኖራል ተብሏል፡፡

ኢራን ድርድሩን እንደምትፈልግ እና ነገር ግን ጥቃት እየተሰነዘረባት ባለበት ሁኔታ ውስጥ እንዳማይሆን መግለጿን ተከትሎ፣ የአውሮፓ ሚኒስትሮች ወደ ድርድሩ ጠረጴዛ ያመጧታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እስራኤል በአንድ ምሽት ብቻ በኢራን ላይ በወሰደቻቸው የአየር ጥቃቶች፣ የኢራን ወታደራዊ ይዞታዎችን ጨምሮ በርካታ ኢላማዎችን መምታቷ የተገለጸ ሲሆን፣ ኢራንም በአጸፋው ወደ እስራኤል ያስወነጨፈቻቸው ሚሳኤሎች አምስት ሰዎችን በማቁሰል፣ በእስራኤል በሚገኘው የማይክሮሶፍት ቢሮ አጠገብ ቃጠሎ መታየቱን የእስራኤል የአደጋ አገልግሎት ጠቅሷል።

ኢራን ከባለፈው እሁድ ጀምሮ በጥቃቶቹ ስለደረሰው ሞት እና ዉድመት ምንም አይነት መረጃ አለመስጠቷን ቢቢሲ ዘግቧል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review