የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከውጪ በሚገቡ የብረት እና የአሉሚኒየም ምርቶች ላይ የጣሉትን 25 በመቶ ታሪፍ ወደ 50 በመቶ ከፍ ማድረጋቸው ተሰምቷል።
ከተሽከርካሪ ምርት ጀምሮ እስከ የጣሳ ምግቦች ምርት ድረስ ጥቅም ላይ የሚውለው ብረት የተጣለበት ታሪፍ፣ ከመጋቢት ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ ጭማሪ እንደተደረገበትም ተመላክቷል።
ታሪፉ፣ የአሜሪካን የብረታብረት ምርት የወደፊት እጣፈንታ አስተማማኝነት ለማረጋገጥ ነው ሲሉ ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል።
የታሪፉን ጭማሪ የተመለከቱ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው፣ የታሪፍ ጭማሪው ከአሜሪካ ውጪ ባሉ ብረታብረት አምራቾች ላይ ከፍተኛ ኪሳራ በማስከተል በንግድ አጋሮች ዘንድ የበቀል እርምጃን እንደሚቀሰቅስ እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።
ታሪፉ፣ በአሜሪካ ላሉ የብረታብረት ተጠቃሚዎች ላይም ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትልባቸው እንደሚችልም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል።
የአሜሪካ ብረታብረት እና አሉሚኒየም አምራቾችም የታሪፍ ጭማሪውን ተከትሎ ምርቱን ማቋረጣቸውንና ደንበኞቻቸው ወደ ፕላስቲክና ወረቀት ምርቶች ፊታቸውን ያዞራሉ የሚል ስጋታቸውን እየገለፁ ነው።
ከአውሮፓ ህብረት ቀጥሎ ሁለተኛዋ ግዙፍ የብረታ ብረት አምራች በሆነችው አሜሪካ የታሪፍ ጭማሪው፣ የንግድ እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደር መጀመሩን እና ከውጪ የሚገቡ የብረት ምርቶች መጠን በ17 በመቶ እንዲቀንስ መንስኤ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
በሊያት ካሳሁን