
AMN – ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም
ዶናልድ ትራምፕ የ2024ቱን የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በማሸነፍ 47ኛው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸውን ገልጸዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በፍሎሪዳ ተገኝተው ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር፣ “ይህ ወሳኝ ክስተት የአሜሪካን ስብራት ለመጠገን ይረዳል” ብለዋል።
“አሁን ወሳኙን የፖለቲካ ግብ አሳክተናል፤ የተፈጠረውን ነገር ተመልከቱ፣ በእጅጉ የሚደንቅ ነው” ሲሉም ስላገኙት ድል የተሰማቸውን ደስታ መግለጻቸውን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል።
“47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኜ በመመረጤ ከፍተኛ ክብር ይሰማኛል፤ የአሜሪካ ሕዝብም ለጣለብኝ አመኔታ ከልብ አመሰግናለሁ” ብለዋል ዶናልድ ትራምፕ።
ከዚህ በፊት የተደረጉባቸውን የግድያ ሙከራዎች በማስታወስም፣ “ፈጣሪ በምክንያት ነው ሕይወቴን ያተረፈው፤ ያ ምክንያት ደግሞ አሜሪካን ለማዳን እና ዳግም ወደ ኃያልነቷ ለመመለስ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
“ከፊታችን ያለው ሥራ ቀላል አይሆንም፤ ነገር ግን ያለኝን ኃይል እና ጉልበት ሁሉ በመጠቀም የጣላችሁብኝን ኃላፊነት ለመወጣት እሰራለሁ” ሲሉም ቃል ገብተዋል።
የአሜሪካ ኮንግረስ 538 ኤሌክቶራል ኮሌጅ ሲኖሩት ከእነዚህ መካከል 270 የሚያገኝ ተፎካካሪ ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እንደሚሆን ይታወቃል።