የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በሪዮ ዴ ጃኔይሮ እየተካሄደ ካለው የብሪክስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጎን ለጎን ከብራዚል እና ሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል።
ዶ/ር ጌዲዮን ከብራዚሉ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማውሮ ቬራ ጋር ባደረጉት ውይይት ብራዚል በብሪክስ የወቅቱ ፕሬዝዳንትነቷ የጀመረችውን ሥራ በማድነቅ ኢትዮጵያ ብራዚል ላስቀመጠቻቸው የብሪክስ የትኩረት አቅጣጫ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
ሚኒስትሮቹ በግብርና ማምረቻ፣በዓለም አቀፍ ተቋማት አስተዳደራዊ ማሻሻያዎች፣በኢነርጂ ሽግግር እና በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።ሁለቱ ሚኒስትሮች የኢትዮጵያ እና ብራዚልን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ተስማምተዋል።
ዶ/ር ጌዲዮን ከሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት የሁለቱን አገራት ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ባደረገ መልኩ ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት ተጨባጭ በሆኑ የትብብር መስኮች ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።