AMN – የካቲት 2/2017 ዓ.ም
በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጉባዔ በኢትዮጵያ መሰረታዊ የሰላም እጦት ስብራቶች ተለይተው ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኙበት አቅጣጫ መቀመጡን የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ታዜር ገብረእግዚአብሄር ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ታዜር ገብረእግዚአብሄር ፓርቲው በሁለተኛ ጉባኤው በሰላምና ጸጥታ ጉዳይ በጥልቅ ተወያይቶ ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጡ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይረጋገጥ ምክንያት ከሆኑት አንዱ የስልጣን ሽግግር የሚደረግበት አግባብ መሆኑ በጥልቅ መገምገሙን ነው የተናገሩት።
ከለውጡ ዓመታት በፊት የነበረው የስልጣን ሽግግር ተቋማትን፣ ሃብትንና የተማረውን የሰው ሃይል ከስርዓት ወደ ስርዓት የሚያሻግር እንዳልነበርም አስታውሰዋል።
ብልጽግና የህዝብ ድምጽ አግኝቶ ወደ ስልጣን ሲመጣ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ባህልን ለማዳበር አዲስ እይታና አስተሳሰብ ማስረጹንም ነው የገለጹት።
ፓርቲው ”ፓርቲዎች ያልፋሉ የሚኖረው አገርና ህዝብ ነው” የሚል ጽኑ እምነት እንዳለው ጠቅሰው፣ ለአገርና ህዝብ ጠቃሚ ነገር ሰርቶ ለማለፍ የስልጣን ሽግግሩን ሰላማዊ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።
ፓርቲው ኢትዮጵያን በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድትቆይ ያደረጉ ገፊ ምክንያቶችን በመለየት ለመፍትሄው ሲተጋ መቆየቱንም ነው ያብራሩት።
በጉባኤው የሰላም እጦት ስብራቶችን በመሰረታዊነት ለመፍታት ሁሉንም ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል አቅጣጫ መቀመጡንም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ህብረ ብሄራዊ ሀገር እንደመሆኗ ብዝሃነት ሲስተናገድበት የነበረው አግባብ የሰላም እጦት መሰረታዊ መነሻ እንደነበር በጉባዔው በሰፊው ውይይት እንደተደረገበት አስታውሰዋል።
ፓርቲው የብሄር ብሄረሰቦችን ብዝሃነት እንደ እሴት በመጠቀም ህብረ-ብሄራዊ አንድነቷ የተጠበቀ አገር ለመገንባት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ፓርቲው ዘመን ተሻጋሪ ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑን ነው የገለጹት።
በኢትዮጵያ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች በርካታ ውጤቶች ቢመዘገቡም አሁንም ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
በጉባኤው በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች ዘላቂና ዋስትና ያለው ሰላምን ለማረጋገጥ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል ውሳኔ መተላለፉን ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ከጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ”ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ሀሳብ ባካሄደው ሁለተኛ ጉባዔ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉ እንደሚታወስ ኢዜአ ዘግቧል።