ጎንደር በአስደማሚ የሽግግር ጉዞ ላይ እንደምትገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገልፀዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፣ ጎንደር በታሪኳ በጥበብ፣ በንግድና በሥልጣኔ ማዕከልነቷ የምናወሳትን ያህል፣ ዛሬም አምራች ኢንዱስትሪን ጨምሮ በአስደማሚ የሽግግር ጉዞ ላይ እንደምትገኝ አይተናል ብለዋል፡፡
በጎንደር ቆይታችን የከተማዋን ውጤታማ የለውጥ ጉዞ የሚያሳዩ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን፣ የፋሲለደስ አብያተ-መንግሥታት እድሳትና ሁለተኛውን ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የሥራ ሂደት ጎብኝተናል ብለዋል አቶ ተመስገን።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን አክለውም፣ በኮሪደር ልማትም በፌደራል መንግሥት ሀሳብ አመንጪነትና አስተባባሪነት የፋሲል ግንብንና የፒያሳ አካባቢን በመጀመሪያው ምዕራፍ በስኬት አጠናቃለች ብለዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማትም ከፒያሳ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያለው መንገድን ጨምሮ በርካታ ልማቶች ጥሩ ሆነው እየተገነቡ መሆኑን ተመልክተናል፤ ጅማሬውና ተነሳሽነቱ እጅግ አስደሳች ነው ብለዋል።
ማህበረሰቡም በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን በግሉ ተነሳሽነት እያደሰ፣ አረንጓዴ ልማትና ፅዱ አካባቢን በመፍጠር ረገድም አበረታች ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብልዋል አቶ ተመስገን።
መልካም ሥራዎችን በማጠናከር መፍጠን ያለባቸውንም እንዲፋጠኑ ለከተማ አስተዳደሩን አቅጣጫ አስቀምጠናል ብለዋል።

እንደሀገር ታሪካችንን አድሰን መጠቀም አለብን ብለን ውጤታማ ሥራ ከሰራንባቸው ሥፍራዎች መካከልም ጎንደር ተጠቃሽ ናት።
የጎንደር አፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥታት እየተደረገላቸው ባለው ሙያዊ እድሳት ግርማ ሞገሳቸው ጎልቶ እየወጣ ከተማዋንም እያፈኩና የቀድሞ ከፍታዋን እየመለሱ ነው ብለዋል።
በመጨረሻም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን፣ የቅርስ ጥበቃና የኮሪደር ልማት ሥራዎቻችን ለመጪው ትውልድ ጭምር ኩራትና ውርስ የሚሆኑ ናቸው፤ ጎንደር ዳግም እየተነሳች ነው ብለዋል።