ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በፈረንሳይ እና ጣሊያን ያደረጉት ጉብኝት ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር በተለያዩ መስኮች ያላትን ትብብር የበለጠ ማጎልበት የሚያስችል ምቹ መደላድል መፍጠሩን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የልዑክ ቡድናቸው ከሰሞኑ በፈረንሳይ እና በጣሊያን የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወቃል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፈረንሳይ እና የጣሊያን ጉብኝትን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በፈረንሳይ በነበራቸው ቆይታ ከፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
በውይይቱ ፕሬዚዳንት ማክሮን በታህሳስ 2017 ዓ.ም ኢትዮጵያን ሲጎበኙ ስምምነት የደረሱባቸው ጉዳዮች ያሉበትን የአፈጻጸም ደረጃ መገምገማቸውን አንስተዋል።
መሪዎቹ ሀገራቱ በኢኮኖሚ፣ በኢንቨስትመንት፣ በመከላከያ፣ በቅርስ ጥበቃ እና በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ነው የፕሬስ ሴክሬታሪያቷ በማብራሪያቸው ያመለከቱት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በየሀገራቱ ያደረጓቸው ጉብኝቶች የሀገራቱ ግንኙነት እንዲጠናከር ማድረጉንም አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በፈረንሳይ በቴክኖሎጂ በተለይም በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በቅርስ ጥበቃ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን መጎብኘታቸውን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጣሊያን ባደረጉት ጉብኝት ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሌኒ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አንስተዋል።
ውይይቱ ሀገራቱ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በኢንቨስትመንት ልማት እና ሌሎች መስኮች ያላቸውን ትብብር እንዲሁም የባለብዙ ወገን ትብብራቸውን ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ያሳዩበት ነውም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከጣሊያኑ ዊ ቢውልድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፔይትሮ ሳሊኒ ጋር ኩባንያው በታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ያለውን ተሳትፎ እና አጠቃላይ ስራ አስመልክቶ መወያየታቸውን አንስተዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አዲስ ከተመረጡት የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሊዮ 14ኛ ጋር በቫቲካን መወያየታቸውንም እንዲሁ።
ጉብኝቱ እና ውይይቱ ኢትዮጵያ ከፈረንሳይ እና ጣሊያን ጋር በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ፣ በመከላከያ እና በቱሪዝም ዘርፎች ያለውን ትብብር የበለጠ ማጠናከር የሚያስችል መደላድል የፈጠረ ነው ብለዋል።
ሀገራቱ በቀጣይ ትብብራቸውን ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከፍ በማድረግ ግንኙነታቸውን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማኖር እንደሚሰሩ መግለጻቸውንም ነው ፕሬስ ሴክሬተሪያቷ ቢልለኔ ስዩም ያብራሩት።