ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ1446ኛው የአረፋ(ዒድ አል አድሃ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንኳን አደረሳችሁ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
እንኳን አደረሳችሁ ለ1446ኛው የአረፋ(ዒድ አል አድሃ) በዓል
በአረፋ በዓል ወቅት የሚታወሱ ሁለት ዕሴቶች፣ ለምንገነባት የበለጸገች ኢትዮጵያ እጅግ በጣም አስፈላጊዎች ናቸው፡፡
የአረፋ በዓል መሥዋዕትነት የሚታሰብበት በዓል ነው፡፡ ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸው ኢስማኤልን በፈቃዳቸው ለፈጣሪ መሥዋዕት ለማድረግ ፍጹም ቆራጥነታቸውን ያሳዩበት በዓል ነው – አረፋ፡፡ ልጅን ለፈጣሪ መሥዋዕት ከማድረግ በላይ መታዘዝም፣መሰጠትም የለም፡፡
ሀገር የምትጸናው በመሥዋዕትነት ነው፡፡ ያውም የምንወደውን ነገር መሥዋዕት በማድረግ፡፡ ሀገር ማለት ቀዳሚው ትውልድ ለተተኪው ትውልድ ሲል መሥዋዕትነት የሚከፍልባት ናት፡፡ ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ለመሥዋዕትነት በማዘጋጀታቸው በምትኩ የሚሠዋ በግ ከአላህ አግኝተዋል፡፡ ሌላ መሥዋዕት ለማግኘት ራስን መሥዋዕትነት ማድረግ ይገባል፡፡ በኢብራሂም ልቡና እስማኤል ተሠዉቷል፡፡ ለሀገሩ የሚሠዋን ትውልድ የሚፈጥረው ለሀገሩ ቀድሞ የተሠዋ ትውልድ ነው፡፡
እናቶቻችንና አባቶቻችን ለሀገራቸው ነጻነትና ሉዓላዊነት መሥዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡ በዚያ መሥዋዕትነታቸው ሰማያዊና ታሪካዊ ዋጋ ያገኙበታል፡፡ ተመጣጣኝ ምድራዊ ምንዳ ግን አያገኙም፡፡ ለሕይወት የሚመጥን ምንም ዓይነት ምንዳ ስለሌለ፡፡ የእነርሱን ምንዳ የምንቀበለው እኛ ነን፡፡ የእኛንም ምንዳ ተተኪው ትውልድ ይመነዳዋል፡፡
አረፋ “ወአረፍተኒ ወአረፍቱ” “አወቅሺኝ፤ ዐወቅኩህ” የተባለበት በዓል ነው፡፡ አደምና ሐዋ ከጀነት ከወጡ በኋላ ለረዥም ዘመን ተለያይተው ኖረዋል፡፡ የተገናኙት በአረፋ ዕለት ነው፡፡ አረፋ የተለያዩ የሚገናኙበት በዓል ነው፡፡ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ አሳዛኙ ነገር መለያየቱ ሳይሆን፣ ተለያይቶ መቅረት ነው፡፡ ሐሳብ፣ አመለካከት፣ ቅሬታ እና ያለፈ ታሪክ በአንድም በሌላም መንገድ አለያይተውን ይሆናል፡፡ ነገር ግን የአንድ ሀገር ልጆች እንደመሆናችን መጠን ተለያይቶ መቅረት ሳይሆን እንደ አደምና ሐዋ የመገናኛ መንገድ ያስፈልገናል፡፡
ለእኛ የመገናኛ መንገዳችን ሀገራዊ ምክክር ነው፡፡ ሀገራዊ ምክክር ሐሳቦቻችን እና ፍላጎቶቻችን የሚገናኙበት መድረክ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን የሚረዳበት፣ አንዱ ሌላውን የሚያስረዳበት፣ አንዱ በሌላው ጫማ የሚቆምበት፣ አንዱ የሌላውን ሕመም የሚታመምበት፤ በመገናኘት “ዐወቅሺኝ፣ ዐወቅኩህ” የምንባባልበት ሰላማዊ መድረክ ነው፡፡
በመሆኑም የአረፋን በዓል ስናከብር ለሀገርና ለነገ ትውልድ የምንከፍለውን መሥዋዕትነት እያሰብን፤ በሀገራዊ ምክክሩም የምንገናኝበትን መድረክ ይበልጥ እያጠናከርን እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በድጋሚ መልካም የአረፋ በዓል ይሁን፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም