ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማዕከላችን ያደረጉት ጉብኝት የአፍሪካ የበሽታ መከላከል ሥራችንን ለማጠናከር ትልቅ አቅም ይፈጥርልናል – የአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር

You are currently viewing ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማዕከላችን ያደረጉት ጉብኝት የአፍሪካ የበሽታ መከላከል ሥራችንን ለማጠናከር ትልቅ አቅም ይፈጥርልናል – የአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር

AMN – መጋቢት 5/2017 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ሲዲሲ ባደረጉት ጉብኝት ያመላከቱን አቅጣጫዎች ለአህጉሪቱ የጤና ስርዓት መጠናከር ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው ሲሉ የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዢያን ካሴያ ገለጹ።

የአፍሪካ የጤና ስርዓት ህልውና ለሆነው የአፍሪካ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል(African CDC) መጠናከር መሪዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከልን(Africa CDC) ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝታቸውም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ የማኅበረሰብ ጤና ተቋም የሆነው የአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል(Africa CDC) መቀመጫ በመሆኗ ክብር ይሰማታል ብለዋል፡፡

በማዕከሉ ያሉት ላቦራቶሪዎች እና የምርምር አቅሞች በበሽታ መቆጣጠር ብሎም በወረርሽኞች እና ተላላፊ በሽታዎች ምላሽ በመስጠት ሥራ ከፍ ያለ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዢያን ካሴያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉብኝት ለማዕከሉ ሰራተኞች ደስታንና በበለጠ ትጋት እንድንሰራ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል(አፍሪካ ሲዲሲ) የአህጉሪቱ የህብረተሰብ ጤና ማዕከል በመሆኑ ትልቅ ሃላፊነት እንዳለበትም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአካል በመምጣት ድጋፋቸውን ማሳየታቸውና ማዕከሉን ወደፊት የሚያራምዱ አቅጣጫዎች መስጠታቸው አስደሳችና ለሌሎች መሪዎች ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የአፍሪካ ሲዲሲ የላብራቶሪ አቅሙን በማሳደግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው ሀገራትን በተሻለ ለማገልግል በከፍተኛ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

አፍሪካ ክትባቶችን ጨምሮ መድኃኒቶችን በራሷ አቅም ማምረት እንዳለባትም ነው የጠቆሙት፡፡

አፍሪካ ሲዲሲ የአፍሪካውያንን ጤና ለማስጠበቅ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረው ለጉብኝት ከሚመጡ መሪዎችም አወንታዊ ሃሳቦች እንደሚሰጠው ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአፍሪካ መሪዎች አኅጉራዊ የማኅበረሰብ ጤና ማዕከሉ የጤና አገልግሎትን እንዲያስፋፋ በሙሉ ኃላፊነት እንዲተባበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጥሪ አቅርበዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review