ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጣሊያን ያደረጉት የስራ ጉብኝት የሁለትዮሽ ትብብሮችን ለማጠናከር የሚያስችሉ ስምምነቶች የተካሄዱበት መሆኑ ተመላከተ

AMN-ግንቦት 19/2017 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጣሊያን ያደረጉት የስራ ጉብኝት የሁለትዮሽ ትብብሮችን ለማጠናከር የሚያስችሉ ስምምነቶች የተካሄዱበት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣሊያን ሮም በነበራቸው ቆይታ ከጣሊያን አቻቸው ጂኦርጂያ ሜሎኒ፤ ከሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሊዮ 14ኛ እና በኢትዮጵያ በታላላቅ ፕሮጀክቶች እየተሳተፈ ከሚገኘው ከWebuild Group ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፔይትሮ ሳሊኒ ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን የጣሊያን ቆይታ አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የልዑካን ቡድኑ አባልና የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ፤ ከጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት የሁለትዮሽ ምክክር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ውይይት አድርገዋል ብለዋል፡፡

በሁለቱ መሪዎች መካከል የተደረገው ውይይት ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርምን ለመደገፍ የጣሊያን መንግስት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ትብብር የተፈጠረበት ነው ያሉት ሚኒስትሩ የጣሊያን ባለሀብቶችም በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

ከWebuild Group ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፔይትሮ ሳሊኒ ጋር በነበራቸው ቆይታም ሰፊ ውይይት ተደርጓል ያሉት አቶ አህመድ ኩባንያው በቀጣይም የቤት ልማት ዘርፍን ጨምሮ በተለያዩ የኢንቨስመንት አማራጮች እንዲሰማራ ግብዣ ቀርቧል ብለዋል፡፡

ከአዲሱ ከሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሊዮ 14ኛ ጋር በነበራቸው ቆይታም በሰላም ጉዳይና በትምህርት ልማት ላይ እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክረው እንዲቀጥሉ መግባባት ላይ ተደርሷል ሲሉ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review