ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ ግዙፍ ዕቃ ጫኝ መርከብ ጓሮዬ ውስጥ ቁሟል

You are currently viewing ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ ግዙፍ ዕቃ ጫኝ መርከብ ጓሮዬ ውስጥ ቁሟል

AMN – ግንቦት 15/2017 ዓ.ም

በማዕከላዊ ኖርዌይ ትሮንደሄም ከተማ ነዋሪ የሆነው ጆሃን ሄልበርግ፣ ትናንት ከእንቅልፌ ስነቃ ቸር አውለኝ ከማለቴ ጓሮዬ ከበደኝ ይላል።

ባይኔስት በተባለችው የባህር ዳርቻ መንደር ነዋሪ የሆነው ጎልማሳው፣ መስኮቴን ስከፍት ጫፉን ዓይቼ የማልጨርሰው ግዙፍ ዕቃ ጫኝ መርከብ አትክልት ስፍራዬ ውስጥ ተገድግዷል ሲል አግራሞቱ ቃላት ያሳጣዋል።

ጆሃን 135 ሜትር ርዝመት ያለው ኮንቴነር ጫኝ መርከብ፣ ማለዳ አካባቢ የጉዞ መስመሩን ስቶ ወደ ቤቱ አቅጣጫ ሲገሰግስ ሲያስተጋባው የነበረውን የማስጠንቀቂያ የጥሩምባ ድምጽ አልሰማም።

ፍጥነቱን መቆጣጠር ያልቻለው ግዙፉ መርከብ የባህር ዳርቻውን አሸዋ አየፈጨ ድንጋያማ ወደ ሆነው ደረቅ መሬት ሲወጣ የጆሃንን ቤት ጥቂት ወደ ቀኝ ስቶት ከጎኑ ይቆማል።

ጆሃን፣ ማለዳ አካባቢ መርከቡ በእርሱ ቤት አቅጣጫ ሲገሰግስ የተመለከቱ ጎረቤቶቹ የቤቱን መጥሪያ ደጋግመው በመደወል ከእንቅልፉ ሊያነቁት ቢሞክሩም “ጥሩ እንቅልፍ በሚወስደኝ የንጋት ሰዓት ሰው ሲቀሰቅሰኝ ስለማልወድ ደውሉን ሰምቼ በር አልከፈትኩም ነበር” ይላል።

በውል ባልታወቀ ምክንያት የጉዞ መስመሩን ስቶ ሰው ደጃፍ ላይ የቆመው ዕቃ ጫኝ መርከብ፣ ባጋጠመው ክስተት ውስጡ በነበሩም ሆነ በአካባባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት አለማድረሱን ቢቢሲ ዘግቧል።

በኢዮብ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review