ከሰሞኑ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የጎበኟቸው የማሌዥያ ሳይበርጃያ እና ፑትራጃያ ከተሞችን በጥቂቱ ለመቃኘት ወደድን።
ሳይበርጂያ
ሳይበርጂያ ከማሌዥያ ውብ ከተሞች መካከል አንዷ ስትሆን የሀገሪቱ የሳይንስ ማዕከል በመሆን ትታወቃለች።
በፈረንጆቹ 2008 ላይ ምርጥ ብሔራዊ የአይሲቲ ማዕከል በመባል ተሸልማለች።
በተማዋ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ልዩ ልዩ የመዝናኛ ሥፍራዎች እና ፓርኮች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የመንገድ መሠረተ ልማቶች፣ የሳይክል እና የእግረኛ መንገዶችም ለምተው ይገኛሉ።
ፑትራጃያ
ፑትራጃያም ሌላኛዋ የማሌዥያ ደማቅ ከተማ ስትሆን ከኩዋላ ላምፑር እና ሳይበርጂያ ከተሞች ጋር ተጎራብታ ትገኛለች።
ከተማዋ ስያሜዋን ያገኘችው ከማሌዥያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበሩት ቱንኩ አብዱል ራህማን ነው። ጊዜውም በፈረንጆቹ 1994 ነበር።
በማላያ ቋንቋ “ፑትራ” ማለት ወንድ ልጅ ማለት ሲሆን “ጂያ” ማለት ደግሞ ድል ወይም ስኬት እንደማለት ነው።
የከተማዋ ሕዝብ ብዛት ከ119 ሺህ በላይ በላይ ሲሆን አብዛኞቹ ነዋሪዎችም የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው።
ከተማዋ በዓመት ውስጥ አብዛኛውን ወራት ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ታገኛለች፤ ይህ ነው የሚባል ደረቃማ የአየር ወቅት የላትም።
የመንግሥት ሠራተኞች ቀደም ሲል ከነበሩባቸው ከተሞች ወደ ፑትራጃያ እንዲገቡ የተደረገው የተለያዩ የድጎማ እና ብድር ሥርዓት በማበጀት ነው።
97 በመቶ የሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች የእስልምና እምነት ተከታዮች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የሒንዱ፣ ክርስትና፣ በድሀ እና የሌሎች ያልታወቁ እምነት ተከታዮች ናቸው።
የፑትራጃያ መሠረተ ልማት ሥራዎች ዲዛይን ከመካከለኛው ምሥራቅ የተቀዱ በመሆናቸው ማሌዥያን የእስልምና መለዮ አላብሷታል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከሰሞኑ የማሌዥያ ዋና ከተማ ኩዋላ ላምፑርን ጨምሮ የፑትራጃያ እና ሳይበርጂያ ከተሞችን ጎብኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች ጉዟቸውን በተመለከተም፣ “የማሌዥያዋ ኳላ ላምፑር ከተማን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ እና በቱሪዝም ልማት እያካሄደች ያለው የትራንስፎርሜሽን ሥራዎች የምንማርበት በመሆኑ የሁለቱን ከተሞች ግንኙነት አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል።” ማለታቸውም ይታወሳል።
በማሬ ቃጦ