AMN – መስከረም 30/2017 ዓ.ም
የዘንድሮው የዓለም ዕይታ ቀን መሪ ሐሳብ “ዐይኖችህን ጠብቅ” በሚል በልጆች ዕይታ እና የዐይን ጤና ልዩ ፍላጎቶች ላይ ያተኩራል።
የዓለም የዕይታ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ24ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ23ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።
ሀገራት በዜጎቻቸው ላይ የሚደርስን የብረሃን ማጣት እና የዕይታ ችግርን ለመቅረፍ ትኩረት እንዲሰጡ ለማስቻል በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፈረንጆቹ 2000 ጀምሮ የዕይታ ቀን እየተከበረ ይገኛል።
በሀገራችን ከፍተኛ የዐይን ጤና ችግር ከሚያስከትሉ በሽታዎች መካከልም የዐይን ሞራ ግርዶሽ፣ በመነጽር የሚስተካከል የዕይታ ችግር፣ ትራኮማ እና በስኳር ሕመም ምክንያት የሚመጣ የዐይን ችግር ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስዱ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በኢትዮጵያ በዐይን ጤና ዘርፍ በተካሄደው ሀገር አቀፍ ጥናት መሠረት ለዐይነ ሥውርነት መንሥኤ ተብለው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል
የዐይን ሞራ ግርዶሽ (Cataract) 50 በመቶ
ትራኮማ (Trachoma) ከ11 በመቶ በላይ
አጥርቶ የማየት እና የዕይታ አድማሱን የሚገድበው ግላኮማ ከ5.2 በመቶ በላይ ለሚሆነው ዐይነ ሥውርነት ምክንያት ሆነው ይጠቀሳሉ።
እስከ 90 በመቶ የሚሆነው የዐይን ጤና ችግር ጉዳት ሳያስከትል መከላከል የሚቻል ነው።
ታክመው ለሚድኑ የዐይን ሕመሞች ትኩረት መሰጠት ደግሞ ሕመሙ እንዳይባባስ እንደ መፍትሔ የሚቀመጥ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ይመክራል።
ሠራተኞች በሥራ ቦታ ለዐይናቸው ጤና ትኩረት እንዲሰጡ ማድረግ እና የሥራ ኃላፊዎችም የሠራተኞቻቸውን የዐይን ጤና በመጠበቅ ምርታማነትን እንዲያሳድጉም የዘርፉ ጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ።
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አሁን አሁን ለዕይታ ሕመም እያጋለጠ ከሚመጣው መንሥኤዎች ዋነኛ እየሆነ የመጣው ረዥም ሰዓት ስክሪን ላይ መቆየት የሚጠቀስ ነው።
ባለሙያዎች እንደሚመክሩት አንድ ሰው በቀን ከ2 ሰዓት በላይ ስክሪን ላይ የሚቆይ ከሆነ በዕይታው ላይ እክል እያጋጠመው ይሄዳል።
ከኢትዮጵያ 1 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች ዐይነ-ሥውራን ሲሆኑ 3 ነጥብ 6 በመቶው የሚሆኑት ደግሞ የዐይን እክል እንዳለባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
ምንጭ፡- ጤና ሚኒስቴር፣ ፕሪቨንት ብላይንድነስ እና ሌሎች ድረገጾች
በሽመልስ ታደሰ