ፀሃይ -2 አውሮፕላን የመጀመሪያ የሙከራ በረራዋን በስኬት አጠናቀቀች

AMN – የካቲት 14/2017 ዓ.ም

በአየር ኃይል ውስጥ የተሰራችው ፀሃይ – 2 የስልጠና አውሮፕላን የመጀመሪያ የሙከራ በረራዋን በስኬት ማከናወን መቻሏን የአየር ኃይል ምክትል አዛዥ የአቭየሽን ከባድ ጥገና ማዕከል ኮሎኔል መሰረት ጌታቸው ገልፀዋል፡፡

ፀሃይ -2 አውሮፕላን ለበረራ ማሰልጠኛ እና ለሌሎች አገልግሎት መዋል የምትችል መሆኑን ያስታወቁት ኮሎኔል መሰረት ጌታቸው የተሰጣትን ግዳጅ በብቃት መፈፀም የሚያስችላትን የዘመኑን የአቭዬሽን ቴክኖሎጂ መታጠቋንም አብራርተዋል፡፡

የአውሮፕላኗ ስኬታማ የሙከራ በረራ አየር ኃይሉ የደረሰበትን የከፍታ ጉዞ ጠቋሚ ነው ያሉት ምክትል አዛዡ በቀጣይነትም ወደ ምርት ሂደት ለመሸጋገር ፋብሪካውን የማደራጀት ፣የመፈተሻ እቃዎችን የማሟላት እና የሙያተኞችን አቅም የማጎልበት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የትራንስፖርት አውሮፕላን ስኳድሮን አዛዥ እና አብራሪ እንዲሁም የፀሃይ -2 የሙከራ በረራን በስኬት ያካሄዱት ሻለቃ ፍቃዱ ደምሴ በበኩላቸው አውሮፕላኗ አለም የደረሰበትን የአውሮፕላን ቴክኖሎጂ የታጠቀች የበረራ አቅሟም አስተማማኝ እና ተቋሙ ለያዘው የወደፊት ራዕይ ጉልህ አስተዋፅዖ የምታበረክት መሆኗን የሀገር መከላከያ ሰራዊት በማህበራዊ ትስስር ገፁ አመለክቷል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review