ፈረንሳይ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ እንደምትደግፍ አስታወቀች

AMN – ታኅሣሥ 13/2017 ዓ.ም

የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኤል ማክሮን በትናትናው ዕለት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በሁለትዮሽ እና ሁለቱ ሀገራት ገንኙነታቸውን ይበልጥ ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።

በውይይታቸውም ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በመነጋገር ላይ የተመሰረተ እና የዓለም አቀፍ ሕግን እና መርሕን የተከተለ የባህር በር ጥያቄን እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄም ይህንኑ ሕግ እና መርሕ የተከተለ በመሆኑ ፈረንሳይ ጥያቄውን እንደምትደግፍ አመልክተዋል።

በቱርክ ፕሬዚዳንት ረሲብ ጠይብ ኤርዶሃን ሸምጋይነት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የደረሱበትን የአንካራ ስምምነት በመልካም ጎኑ እንደሚመለከቱትም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።

ሁለቱ ሀገራት ስምምነቱን በማክበር ለተግባራዊነቱ መሥራት እንዳለባቸውም ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አሳስበዋል።

ለኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄም ፈረንሳይ አስፈላጊውን ድጋፏን እንደምታደርግ ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ይሳካ ዘንድም ፈረንሳይ ያላሰለሰ ጥረት እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ትክክለኝነት እና ሕጋዊነት መገንዘባቸውን በሰጡት አስተያየት ገልጸው ለዚህም ድጋፍ እንደሚያደረድጉ መስማማታቸውን አክለዋል።

የሁለቱ ሀገራ ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን የፕሪቶሪያውን ስምምነት በመልካም ጎኑ አንሥተዋል።

ፈረንሳይ ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዕድሳት ድጋፍ ማድረጓን እና ይህም የገንዘብ እና የቴክኒክ እገዛ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዚዳንቱ ማስረዳታቸውን ቪኦኤ ዘግቧል።

ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፈረንሳይ መንግሥት የ25 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ የታደሰውን እና በቅርቡ ለሕዝብ ክፍት የሚሆነውን የብሔራዊ ቤተመንግሥትንም ጎብኝተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review