AMN-የካቲት 28/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣ ከአከባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመቀናጀት በዛሬው ዕለት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ፍሳሽ ቆሻሻን በመልቀቅ ወንዝ በመበከል ደንብ ተላልፎ በተገኘ ድርጅት ላይ 300 ሺህ ብር በመቅጣት አስተዳደራዊ እርምጃ ወስዷል።
ድርጅቱ በደንብ ቁጥር 180/17 የቅጣት ሰንጠረዥ 1 ተራ ቁጥር 3 ያልተጣራ ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዝ ስለመልቀቅ የወጣውን ደንብ በመተላለፍ ቅጣቱ እንደተጣለበት ገልጿል፡፡
ባለስልጣኑ በደንብ ቁጥር 180/2017 ላይ ከአከባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙኃን እና በመድረኮች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠሩንም አመላክቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ በጀት በመመደብ ከተማዋን ውብ ጽዱና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የወንዝ ዳርቻና የኮሪደር ልማት 7/24 በመስራት የወንዞች ዳርቻ የማስዋብ ስራዎችን እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።
ህብረተሰቡም መንግስት ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ ያለማቸውን ሀብቶች እንዲንከባከብና ደንብ ተላልፎ የሚገኝ አካል ሲገኝ በ9995 ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪውን አቅርቧል።
ባለስልጣኑ በቀጣይ በየትኛውም የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ዙሪያ የሚደረጉ የደንብ መተላለፎችን እንደማይታገስና እርምጃውንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማሳወቁን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ኮሙኔኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።