AMN – መጋቢት 10/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ በተለምዶ ቀይ ባህር ኮንዶሚኒየም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የህዝብ መዝናኛ ስፍራ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ ለአዲስ አበባ ተጨማሪ ውበት እንደሆነ ተገለጸ፡፡
ከእንጦጦ እስከ ፍሬንድሽፕ የወንዝ ተፋሰስ ዳርቻ ልማት አካል የሆነው ይህ የህዝብ መዝናኛ ስፍራ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።
የመዝናኛ ስፍራው በውስጡ የተለያዩ የአገልግሎት መስጫዎችን የያዘ ሲሆን፣ ፋውንቴን፣ የካፍቴሪያ አገልግሎት፣ የመጸዳጃ ቤትና ሌሎችንም እንዳካተተ ነው የተመላከተው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና የአረንጓዴ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ፣ አካባቢው ከዚህ ቀደም አስቸጋሪና ወንጀል የሚፈፀምበት መሆኑን አንስተው፣ አሁን ገጽታው ተቀይሮ ምቹ እና ለአዲስ አበባ ተጨማሪ ውበት የሰጠ፣ ለነዋሪውም እፎይታን ያመጣ ነው ብለዋል።

የመዝናኛ ስፍራው ለሰርግ፣ ለልደትና ለልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች መከወኛ ጭምር እንዲውል ታስቦ መገንባቱንም አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች አስተዳደር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነጻነት ዳባ በበኩላቸው፣ የለማው ቦታ ለህዝብ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ተደርጎ የተገነባ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይ አካባቢው ቀይ ባህር ኮንዶሚኒየም እንደመባሉ ይህንን የሚገልጽ ስያሜ እንዲኖረው ታስቦ ቀይ ባህር የህዝብ የመዝናኛ ቦታ የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ጠቁመዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚዋ አክለውም ልማቱ በአጭር ጊዜ በ24/7 በመስራት ውብ፣ አረንጓዴ በተላበሰ መልኩ ደረጃውን ጠብቆ የለማ ሲሆን አሁን ላይ ውብ ገፅታ እንዲኖረው አስችሏል ብለዋል።
በምሽትም ሆነ በቀን እንደልብ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ እንደነበር የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎችም፣ በርካቶችን ለዝርፊያና አለፍ ሲልም ለሞት የዳረገ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ እንደልባቸው እንዲንቀሳቀሱ ያስቻለና ለልጆቻቸው አማራጭ የመዝናኛ ስፍራ መሆኑ እንዳስደሰታቸው አክለዋል።
በሄለን ጀንበሬ